ከመንግሥት ድጎማ ወደ ገበያ ተወዳዳሪነት፦ የኢትዮጵያ መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች ሽግግር - ኢዜአ አማርኛ
ከመንግሥት ድጎማ ወደ ገበያ ተወዳዳሪነት፦ የኢትዮጵያ መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች ሽግግር
በሙሴ መለሰ
ኢትዮጵያ ግዙፍ የመንግሥት የልማት ድርጅቶቿን (SOEs) በማሻሻል ረገድ ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ዳይሬክተር መሪየም ሳሊም “From Fiscal Burden to Job Engine: Ethiopia’s State-Owned Enterprise Transformation” በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ጽሑፍ እንደገለጹት፤ እነዚህ ተቋማት ቀደም ሲል ለሀገር ኢኮኖሚ ከባድ የገንዘብ ሸክም የነበሩ ቢሆንም፣ አሁን ግን ወደ ኢኮኖሚው ሞተርነትና የሥራ ዕድል ፈጣሪነት እየተሸጋገሩ ነው።
ይህም መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ቀጥተኛ ሚና በመቀነስ የግል ዘርፉን ለማሳደግ የያዘው ስትራቴጂያዊ ግብ አካል ነው። የዚህ ለውጥ ፍሬ በተጨባጭ ቁጥሮች መታየት ጀምሯል። በ2024-2025 የዘጠኝ ወራት የበጀት ዓመት ብቻ እነዚህ ድርጅቶች 98 ቢሊዮን ብር ($600 ሚሊዮን) ታክስ እና 19 ቢሊዮን ብር ($120 ሚሊዮን) የትርፍ ክፍያ ለመንግሥት ገቢ አድርገዋል። ይህ የተገኘ ሀብት ለደመወዝ ክፍያ፣ ለኤሌክትሪክ አቅርቦትና ለሕዝባዊ አገልግሎቶች የሚውል ተጨማሪ አቅም ከመፍጠሩም በላይ፣ በብሔራዊ በጀቱ ላይ የነበረውን ከፍተኛ ጫና ማቃለል መቻሉን መሪየም ሳሊም አመልክተዋል።
ከዓመታት በፊት የነበረው ሁኔታ ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነበር። ድርጅቶቹ ራሳቸውን ችለው ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ገቢ ባለማመንጨታቸው በመንግሥት ላይ ጥገኛ ነበሩ። እ.ኤ.አ. በ2021 የወጣ የዓለም ባንክ ግምገማ እንደሚያሳየው፣ ከ2013 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት የ41 የፌዴራል የልማት ድርጅቶች የተጣራ ሀብት ቢያድግም ትርፋማነታቸው ግን እያሽቆለቆለ ነበር።
ብዙዎቹ የኦዲት ሪፖርት የሌላቸውና ለዓመታት የፋይናንስ መግለጫ ያላወጡ በመሆናቸው፣ ውሳኔዎች ያለ በቂ መረጃ የሚሰጡበትና ኪሳራን በበጀት የመሸፈን አሳሳቢ ሥርዓት ተፈጥሮ ነበር። ይህንን ምስቅልቅል ሁኔታ ለመቀየር የሕዝብ ሀብት አስተዳደር ሥርዓቱን እንደገና ማስተካከል የግድ አስፈላጊ ሆነ።
መንግሥት ያለውን ሀብት ጠንቅቆ እንዲያውቅ፣ ድርጅቶቹ የሚመሩበትን መንገድ እንዲቆጣጠርና የፋይናንስ ስጋቱን በአግባቡ እንዲይዝ የሚያስችል የአሠራር ለውጥ መተግበር ጀመረ። ይህም ድርጅቶቹ በሚያስመዘግቡት ውጤት ተጠያቂ እንዲሆኑ መንገድ መክፈቱን ዳይሬክተሯ መሪየም ሳሊም ያምናሉ።
ዛሬ ላይ አብዛኞቹ የፌዴራል የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ መግለጫዎቻቸውን በወቅቱ ማውጣት ጀምረዋል። የውጭ ኦዲት ሥራቸውን አጠናቀው ውጤቱንም ይፋ ማድረጋቸው፣ የአፈጻጸም ደረጃቸውን ለመከታተልና የኢንቨስትመንት ውሳኔዎችን በዕውቀት ላይ ተመስርቶ ለመምራት የሚያስችሉ መደበኛ ግምገማዎች እንዲጀመሩ ማድረጉን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
እነዚህ ማሻሻያዎች በኢኮኖሚው ላይ ብቻ ሳይሆን በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይም ተስፋ እየፈነጠቁ ነው። በተሻለ ሁኔታ የሚመሩና የፋይናንስ መረጋጋት ያላቸው ድርጅቶች አገልግሎቶቻቸውን ለማስፋፋትና በአዳዲስ ዘርፎች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ በመቻላቸው፣ ለክህሎት ልማትና ለአዳዲስ የሥራ ዕድሎች ትልቅ በር እየከፈቱ ይገኛሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ስኬት የሚያሳየው ጠንካራ የመንግሥት አመራር ከተመረጠ ድጋፍ ጋር ሲቀናጅ የሚኖረውን ውጤት ነው። የመንግሥት ሀብትን ከአስተዳደር ማሻሻያ እና ከልማት ግቦች ጋር በማጣጣም፣ ሀገሪቱ ለሥራ ዕድል ፈጠራና በግል ዘርፍ ለሚመራ ዕድገት አዳዲስ መንገዶችን እየተከተለች ነው። ይህ መሻሻል በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው የሪፎርም ውጤት ነው። እ.ኤ.አ. በ2019 በዓለም ባንክ ድጋፍ የተጀመረው ፕሮግራም፣ የገንዘብ ሚኒስቴር የመጀመሪያውን አጠቃላይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የመረጃ ቋት (Database) እንዲገነባ ማስቻሉን ዳይሬክተሯ መሪየም ሳሊም ጠቁመዋል።
ይህም ፖሊሲ አውጪዎች የእያንዳንዱን ኩባንያ ገቢ፣ ወጪና ዕዳ በግልጽ እንዲያውቁ ረድቷል። ከመረጃ ጥራት ቀጥሎ ትኩረቱ ወደ ድርጅቶቹ የአመራር ሥርዓት ዞረ። እ.ኤ.አ. በ2020 የወጣው አዲሱ የፕራይቬታይዜሽን አዋጅ ለግልጽነትና ለሂደት ደንቦችን በማስቀመጥ፣ በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የነበረውን የግል ፍላጎት ተጽዕኖ መቀነስ ችሏል። ሌላው ትልቅ ተቋማዊ እርምጃ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH) መመሥረት ነው። ይህም መንግሥት የሕዝብ ሀብትን በስትራቴጂካዊና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲያስተዳድር ማስቻሉን መሪየም ሳሊም በጽሑፋቸው አንስተዋል።
አዲሱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዋጅ ድርጅቶቹ በሙያዊ ብቃት እንዲመሩ፣ ከግል ኩባንያዎች ጋር በፍትሐዊነት እንዲወዳደሩና ዓለም አቀፍ የሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎችን (IFRS) እንዲከተሉ አስገድዷል። እነዚህ ለውጦች በተግባር ውጤት እያሳዩ መሆናቸውን በምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።
የኢትዮጵያ ፖስታ ከዓመታት ኪሳራ ወጥቶ ጠንካራ አፈጻጸም ካላቸው ድርጅቶች አንዱ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ደግሞ በግብርናው ዘርፍ የግል ባለሀብቶች የሚያጋጥሟቸውን እንቅፋቶችን ለማስወገድ በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል።
ወደፊትም የተመረጡ ድርጅቶች አክሲዮኖቻቸውን በካፒታል ገበያ ላይ ለማውጣት ያላቸው ዝግጁነት እየተገመገመ ነው። የዚህ ዓላማ የግል ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና በገበያው መስፈርቶች አማካኝነት በንግድ ድርጅቶች አሠራር ውስጥ የላቀ ሥርዓትና ግልጽነትን ማስፈን መሆኑን መሪየም ሳሊም ገልጸዋል።
የሪፎርም አጀንዳው ድርጅቶቹ የያዙትን መሬት፣ መሣሪያዎችና ንብረቶች በሥርዓት መገምገምን ያካተተ ነው። ይህም የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሀብት አስተዳደር መመሪያ እንዲወጣ በማድረግ፣ ንብረቶች በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ መሠረት ጥሏል። በአጠቃላይ እነዚህ ማሻሻያዎች የፋይናንስ አፈጻጸምን ከማሻሻል ባለፈ የሕዝብ ሀብት ለኢኮኖሚ ሽግግሩ ያለውን አስተዋፅኦ በማሳደግ ላይ ይገኛሉ።
ጠንካራና ግልጽ ድርጅቶች የግል ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ለሥራ ዕድል ፈጠራ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ የልማት ድርጅቶችን ዘመናዊ የማድረግ ትኩረቷ ስጋትን ከመቆጣጠር ዕድሎችን ወደ መጠቀም እያሸጋገራት እንደሚገኝ ዳይሬክተሯ መሪየም ሳሊም ገልጸዋል።
ይህም ድርጅቶቹ ራሳቸውን ችለው በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን ሲጀምሩ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የእድገት እና የልማት ጉዞ የሚያፋጥኑ እንደሚሆኑ በጽሁፋቸው ማጠቃለያ ላይ አስፍረዋል።