የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ በትኩረት መስራት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ በትኩረት መስራት አለባቸው
ደብረ ብርሃን፤ መጋቢት 28/2018 (ኢዜአ)፡- የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ተመላከተ።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአራት የጤና ዘርፎች የመማር ማስተማርና የምርምር ስራዎች ጥራት ከኢትዮጵያ ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን እውቅና አግኝቷል።
የኢትዮጵያ ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የእውቅና መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተረፈ በላይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሚሰጧቸው የትምህርት ዘርፎች ጥራትን በማስጠበቅ ተወዳዳሪ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ባለስልጣኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከመማር ማስተማር ስራቸው ጎን ለጎን በምርምርና በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የህብረተሰቡን ችግር በመፍታት ረገድ የሚያስመዝግቡት ውጤት የተጀመረውን የውድድር መንፈስ መፍጠር አጠናክሮ ያስቀጥላል ብለዋል።
ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም የእውቅና ሰርተፊኬት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲም ያገኘውን ውጤት ለማስቀጠልና በሌሎች ዘርፎች ተጨማሪ እውቅና ለማግኘት መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ ትምህርት ዴስክ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ነገዎ በእውቅና አሰጣጡ መድረክ ላይ እንደገለጹት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በትምህርት ጥራት ማስጠበቅና በምርምር ስራ ሊወዳደሩ ይገባል።
የሚሰጧቸው የትምህርት ዘርፎችም አለም አቀፍ ስታንዳርዱ የሚጠይቀውን የጥራት ደረጃ ማሟላት በሚያስችል መልኩ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲም በጤናው ዘርፍ ባስመዘገበው የጥራት ማስጠበቅ ተግባር የእውቅና ሰርተፊኬት ማግኘቱ በሌሎች ፕሮግራሞች ተግቶ እንዲሰራ ተነሳሽነትን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስማረ መለሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ የመማር ማስተማርና የምርምር ዘዴን በመከተሉ ለውጤት መብቃቱን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በ36 የትምህርት ዘርፎች በርካታ የሰው ሃይል በማሰልጠን የአገራችንን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ለማስቀጠል የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም በጤናው ዘርፍ በአኔስቴዥያ፣ በአዋላጅ ነርስ፣ በሜዲስንና በነርሲንግ የትምህርት መስኮች እውቅና ለማግኘት መብቃቱን ጠቁመው ይህም በቀጣይ በሌሎች የትምህርት ዘርፎች የተሻለ ለመስራት መነሳሳትን ይፈጥራል ብለዋል።
ለዩኒቨርሲቲው የተሰጠው ዕውቅናም እስከ 5 ዓመት የሚቆይ መሆኑም ተመላክቷል።