በአስተዳደሩ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ እየተደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአስተዳደሩ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ እየተደረጉ ነው
ድሬዳዋ፤ መጋቢት 29/2018 (ኢዜአ) ፡-በድሬዳዋ አስተዳደር የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ እየተደረጉ መሆናቸው ተገለጸ።
የትንሳኤ በአልን ምክንያት በማድረግ ከ50 በላይ ሞዴል ኢንተርፕራይዞች የተሳተፉበት የንግድ ኤግዚቢሽንና ባዛር ዛሬ በድሬዳዋ በይፋ ተከፍቷል።
የተዘጋጀውን ባዛር የከፈቱት የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን፣ የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ናቸው።
በወቅቱም አቶ ሮቤል ጌታቸው እንዳሉት፤ የትንሳኤ በአልን ምክንያት በማድረግ የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ የማቅረብ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት ምርትና ምርታማነታቸውን እያሳደጉ የሚገኙ ከ50 በላይ ሞዴል ኢንተርፕራይዞች የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለገበያ መቅረባቸውን ገልጸዋል።
በአለም ወቅታዊ ሁኔታ የተከሰተውን የንግድ እንቅስቃሴዎች መዛባት ተከትሎ የሚስተዋለውን የሸቀጦች ዋጋ ንረት ለመከላከል በሰንበት ገበያዎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ኤግዚቢሽኑና ባዛሩ ሸማቾችን ከሞዴል ኢንተርፕራይዞች ጋር በማገናኘት ዘላቂ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ማድረጉን አስረድተዋል።
በባዛሩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ሸማቾችና ሞዴል ኢንተርፕራይዞች በበኩላቸው የተዘጋጀው ባዛር የንግዱን ማህበረሰብ ከሸማቾች ጋር ያስተሳሰረ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
አቶ ኢዘዲን ሱልጣንና ወይዘሮ አስናቀች ፈንታ እንዳሉት፤ ምርቶችን ከመደበኛው የገበያ ዋጋ ባነሰ ማቅረባቸው ለሸማቾች አማራጭ ግብይት ለማካሄድ ያስችላቸዋል።
የአስተዳደሩ ንግድ ፅህፈት ቤት ከቢሮው ጋር በመቀናጀት በተለያዩ ቦታዎች የገበያ ስፍራዎችን በማዘጋጀት የገበያ የማረጋጋት ስራ መስራት እንዳለበትም አመልክተዋል።
በስፍራው ተገኝተው የተለያዩ ምርቶችን የሸመቱት ወይዘሮ የውብዳር አክሊሉ በአስተዳደሩ የተዘጋጀው ኤግዚቢሽንና ባዛር ሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን ለመሸመት እንዲችሉ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።