ሀገራዊ ለውጡ ዜጎች በሀገራቸው ያላቸው ተስፋና እምነት እንዲለመልም አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ለውጡ ዜጎች በሀገራቸው ያላቸው ተስፋና እምነት እንዲለመልም አድርጓል
ጂንካ፤መጋቢት 29/2018(ኢዜአ):- ሀገራዊ ለውጡ ዜጎች በሀገራቸው ያላቸው ተስፋና እምነት እንዲለመልም ማድረጉን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ ገለፁ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ሀገራዊ ለውጡን የሚዘክር ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄዷል ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ በጂንካ ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ያለፉት ስምንት ዓመታትን ‹‹በፈተናዎች የታጀቡ ነገር ግን በስኬት የተቋጩ›› ሲሉ ገልፀዋቸዋል።
በሀገራዊ ለውጡ በፖለቲካው ምህዳር አንዱ ቤተኛ ሌላው አጋር የሚሆንበት የፖለቲካ አውድ ተቀይሮ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ እኩል ውሳኔ የሚሰጡበት አውድ ተፈጥሯል ነው ያሉት።
በዚህም ሀገራዊ ለውጡ ዜጎች በሀገራቸው ያላቸው ተስፋና እምነት እንዲለመልም አድርጓል ብለዋል።
ሀገራዊ ለውጡ አሳሪ የሆነ የፖለቲካ ባህል ተቀይሮ በምትኩ ነፃ፣ አሳታፊ፣ አካታችና የሀሳብ ልዩነቶችን ያከበረ የፖለቲካ ምህዳር የተፈጠረበት መሆኑንም አንስተዋል።
በሀገራዊ ለውጡ ልመናን የሚፀየፍ ትውልድ መፈጠሩን ገልፀው፥ ትውልዱ የእርዳታ ስንዴን መቀበል ሳይሆን አምርቶ ወደ ውጭ መላክን ተምሯል ነው ያሉት።
የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ በበኩላቸው ሀገራዊ ለውጡ አካታችና ለህብረ ብሔራዊ አንድነት እውቅናን የሰጠ ስለመሆኑመ አንስተዋል።
በሀገራዊ ለውጡ ዜጎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸው ተከብሮ ፍትሀዊ ተጠቃሚነታቸው መረጋገጡን አመልክተዋል።
በለውጡ ዓመታትም ጂንካን እናልማ በሚል መሪ ሀሳብ ህዝቡን በማሳተፍ በከተማዋ የተጀመሩ የኮሪደርና የመልሶ ማልማት ስራዎች ተጨባጭ ለውጦች ማምጣት ችለዋል ያሉት ደግሞ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ደግፌ ጌታቸው ናቸው።
የጂንካ ከተማ በለውጡ ዓመታት ባገኘችው የመልማት እድል ፈጣን እድገት በማሳየት ላይ መሆኗንም ጠቁመዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተሳተፉት የጂንካ ከተማ ነዋሪው አቶ ሳሙኤል ጎታ እና ሰላም ኃይሌ፥ ሀገራዊ ለውጡ ከጨለማ ወደ ብርሃን የተሸጋገርንበት ነው ብለዋል።
በሀገራዊ ለውጡ በሀገራችን ላይ ያለን እምነት እና ተስፋ ለምልሟል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፥ ይህንን ለውጥ ለማስቀጠልም ሁለንተናዊ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
በጂንካ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይም ለሀገራዊ ለውጡ እውቅና የሚሰጡ በርካታ መልእክቶች ተላልፈዋል ።