በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመታገዝ ህክምና ለመስጠት የተከናወነው የሙከራ ትግበራ ስኬታማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመታገዝ ህክምና ለመስጠት የተከናወነው የሙከራ ትግበራ ስኬታማ ነው
አርባ ምንጭ፤ መጋቢት 29/2018 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመታገዝ ህክምና ለመስጠት የተከናወነው የሙከራ ትግበራ ስኬታማ መሆኑ ተገለጸ።
የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በምዕራብ አባያ ወረዳ በሚገኝ ጤና ኬላ በመገኘት የሰው ሰራሽ አስተውሎት በመታገዝ እየተከናወነ ያለውን የህክምና የሙከራ ትግበራ የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
ሚኒስቴሩ ከ"ላስት ማይል ሄልዝ" ጋር በመተባበር ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ስራ አጋዥ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በማጎልበት በሀገሪቱ በ7 ክልሎች በሚገኙ 15 ወረዳዎች ላይ የሙከራ ትግበራ ሲያከናውን ቆይቷል።
በዚህ ወቅትም በጤና ሚኒስቴር የዲጅታል ጤና መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ገመችስ መልካሙ እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ በዲጂታል ስርዓት በመታገዝ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።
በዚሁ መሠረትም በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ "የሰው ሰራሽ አስተውሎት"ን በመጠቀም ጥራት ያለው የጤና ስርዓት ለመገንባት እየሠራ ነው።
በዚሁም ባለፉት ሁለት ወራት በ9 ሺህ ጤና ኬላዎች 31 ሚሊዮን አባዎራዎች ቤተሰብን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ይህም የመረጃ አያያዝ ስርዓትን በማጠናከር በጤና ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በኤ አይ ቴክኖሎጂ የታገዘ ህክምና ለመስጠት ያለመ ነው ያሉት።
በዚህም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምን የሚያሻሽል 'የኤሌክትሮኒክስ ኮሙዩኒቲ ሄልዝ ኢንፎርሜሽን ሲስተምና ሄፕ አሲስታንስ' የሚባሉ ሁለት ሶፍትዌሮች ስራ ላይ መዋላቸውን ገልጸዋል።
'የላስት ማይል ሄልዝ' ሲኒየር ፕሮግራም ማኔጀር ዶክተር ሩት ድሪባ በበኩላቸው ጤና ኤክስቴንሽኖች በቀበሌያቸው የሚገኙ ነዋሪዎችን የጤና ሁኔታ በመከታተል እንዲሁም በህክምናው ሂደት የሚገጥማቸውን ጉዳዮችን ኤ አይን በመጠየቅ ምላሽ የሚያገኙበት ስርዓት መዘርጋቱ የጤና አገልግሎትን ለማሳለጥ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
ዓላማውም ሩቅ ያሉ ማህበረሰቦችን በመድረስ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑና በሪፈር ምክንያት ህብረተሰቡን ከእንግልትና ወጪ ለመታደግ መሆኑንም አመልክተዋል።
የኤ አይ ቴክኖሎጂ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ፓኬጆች በምሉዕነት እንድናገለግል አስችሎናል ያለችው ደግሞ በጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ ላዮ ትርጋ ጤና ኬላ ባለሙያ ፍቅሬ ፋርጎ ናት።
ከዚህ ቀደም በርካታ ህሙማንን ወደ ጤና ጣቢያ ሪፈር ለማድረግ እንደሚገደዱ ጠቅሳ አሁን ግን በኤ አይ ቴክኖሎጂ በመታገዝ አገልግሎት መስጠት በመጀመራችን የሪፈር ቁጥር እንዲቀንስ ማድረጉን ገልጻለች።
ከተገልጋዮች መካከል የምዕራብ አባያ ወረዳ ላትርጋ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ደመቀች ስብሎ በበኩላቸው ጤና ኬላው በሚሰጠው አገልግሎት ከእንግልት እና ካለ አስፈላጊ ወጪ ታድጎናል ብለዋል።