በፀጥታ ተቋማት የሪፎርም ሥራዎች የፖሊስ ተቋማዊ አቅም ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል - ኢዜአ አማርኛ
በፀጥታ ተቋማት የሪፎርም ሥራዎች የፖሊስ ተቋማዊ አቅም ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል
አዲስ አበባ፤መጋቢት 29/2018 (ኢዜአ)፦ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የፀጥታ ተቋማት የሪፎርም ሥራዎች የፖሊስን ተቋማዊ አቅም ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገራቸውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ገለፁ።
20ኛው የፌዴራል እና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች ጉባኤ "ፖሊሳዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በጉባኤው የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የፌደራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት፥ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች የፖሊስን ተቋማዊ አቅም ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዳሸጋገሩት ገልጸዋል።
ኮሚሽነር ጄኔራሉ እንዳሉት፣ የጸጥታ ተቋማት ሪፎርም ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ፖሊስ በሰው ኃይል፣ በስልጠና እና በሎጂስቲክስ ረገድ ትልቅ ለውጥ አስመዝግቧል።
ፖሊስ ከዚህ ቀደም ከቴክኖሎጂ ጋር የነበረው ቁርኝት ዝቅተኛ ነበር፤ አሁን ግን በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚ የሆኑና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ምሳሌ የሚወሰዱ ዘመናዊ የወንጀል መከላከልና ምርመራ ቴክኖሎጂዎች ባለቤት መሆን ችሏል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ እና የክልል ፖሊስ አካዳሚዎች በሰጡት ሰፊ ስልጠና፣ ሠራዊቱ በዕውቀት የተገነባ እና ሙያዊ ብቃቱ የተረጋገጠ ፕሮፌሽናል ኃይል እንዲሆን ማስቻሉንም አብራርተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የለውጥ መሪነት የኢትዮጵያ ፖሊስ ዶክትሪን እንዲኖረው፣ የሀገሪቱ የፖሊስ ኃይሎች ወጥ የሆነ፣ መሪ ሀሳብና ስትራቴጂካዊ ራዕይ እንዲኖራቸው መደረጉንም አንስተዋል።
በተጨማሪም በፌዴራል ደረጃ የተገነቡ የሎጂስቲክስ አቅሞች ወደ ክልሎች እንዲስፋፉ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ አብዛኞቹ ክልሎች አሁን ላይ የራሳቸውን የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት ወደሚችሉበት ደረጃ እየተሸጋገሩ ነው ብለዋል።
ጉባኤው በዋናነት በቀጣይ በሚከናወኑ ትላልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር የጋራ አቋም እንደሚይዝም አንስተዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ ፖሊስ የሚጠበቅበትን ከፍተኛ ኃላፊነት ለመወጣት ያለውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እንደሚገመግምም ጠቁመዋል።
ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ አክለውም፣ ሽብርተኞችና ጽንፈኞች ከውጭ ጠላቶች ጋር በመቀናጀት በሀገር ላይ የሚጋርጡትን አደጋ ለማክሸፍ ፖሊስ ከሀገር መከላከያ እና ከደህንነት ተቋማት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
መንግሥት በለውጥ እርምጃዎች ለፖሊስ ሠራዊቱ ዘመናዊ ትጥቅ፣ ሎጂስቲክስ እና በቴክኖሎጂ የተደራጀ እንዲሆን ላደረገው ከፍተኛ ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።