ቀጥታ፡

ከለውጡ ወዲህ የፖሊስ ተቋማት የሀገርን ደኅንነትና የሕዝብን ሰላም በማፅናት የሚያኮራ ተግባር ፈፅመዋል

አዲስ አበባ፤መጋቢት 29/2018 (ኢዜአ)፦ከለውጡ ወዲህ የፖሊስ ተቋማት አንድነታቸውን በማጠናከር የሀገርን ደኅንነትና የሕዝብን ሰላም በማፅናት የሚያኮራ ተግባር መፈጸማቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።

20ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነሮች ጉባኤ “ፖሊሳዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።


 

ጉባኤው በፌዴራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 720/2004 መሠረት የተቋቋመ ሲሆን፣ የፌዴራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች በየራሳቸው ያላቸው ነፃነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ቅንጅት ለማጠናከር ያለመ ነው። 

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የፖሊስ ተቋማት ለሀገር ሉዓላዊነትና ለሕዝብ ደኅንነት ትልቅ ሚና እያበረከቱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ከ2010 ዓ.ም ወዲህ የተከናወነው የፖሊስ ዘርፍ ሪፎርም ዋና ዓላማ ጠንካራ ተቋም መገንባትና በቴክኖሎጂ የታገዘ ብቁ ባለሙያ ማፍራት ነው።

የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያ ፖሊስ በሚሰጠው አገልግሎት ታማኝም አሳማኝም መሆን አለበት ብሎ እንደሚያምን ጠቅሰዋል።፡

የመጀመሪያው ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝቡ እና ለኅሊናቸው ታማኝ በመሆን የተጣለባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት መወጣት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ፖሊስ የሚሠራው ሥራ አሳማኝ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፥  የሚያከናውነው የጸጥታ ጥበቃ ሥራ፣ የሚወስደው ሕጋዊ ርምጃ፣ የወንጀል መከላከል እና ምርመራ ሥራ ለሕዝቡ አሳማኝ በሆነ የላቀ ሥነምግባርና ሞራል መከናወን እንደሚገባው ተናግረዋል።

ይህም ሕዝቡ ለፖሊስ መረጃ በመስጠትና የሰላም ጥበቃው አካል በመሆን በንቃት እንዲሳተፍ የሚያደርግ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።

የፖሊስ ሪፎርም ተጨባጭ ውጤት እያሳየ  ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥  ባለፉት ጊዜያት በባንዳና ባዳ ኃይሎች በሀገርና ሕዝብ ላይ የተቃጡ ጥፋቶችን፣ የፖሊስ ኃይላችን በአንድነት ቆሞ መሥዋዕትነት በመክፈል ጭምር ኢትዮጵያን አጽንቷል ብለዋል።

ፖሊስ የጠላትን ተልዕኮ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ ሠርጎ ገቦችን በማደንና በቁጥጥር ስር በማዋል፣ የሀገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያለ ዕንቅፋት እንዲቀጥል ማድረጉም የሪፎርሙ አንኳር ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህ ደግሞ የፖሊስ አመራርና እና የሠራዊቱ አባላት ያላቸው ሚና የማይተካ ነው ብለዋል።


 

ፖሊስ ቀጣይ ብዙ ሀገራዊ ተልዕኮዎች እንዳሉት በማንሳት በመጪው ግንቦት ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ  ምርጫ ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ገልጸዋል።

ምርጫው ሦስት ዋና ዋና ሀገራዊ ግቦች እንዳሉት ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት አንድ እርምጃ ማራመድ፤ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሀገረ መንግሥቱን ቀጣይነት ማረጋገጥና ምርጫውን በማደናቀፍ ሀገርን ያለ መንግሥት ለማስቀረት የሚሸረቡ የውስጥና የውጭ ሴራዎችን ማክሸፍ ናቸው ብለዋል።

ለዚህ ስኬት ፖሊስ የምርጫውን ሂደት በንሥር ዓይን በመከታተል፣ ተሳታፊዎችን ከማንኛውም ጥቃት የመጠበቅና ስጋቶችን ማምከን እንዳለበት ተናግረዋል።

ለዚህም ማኅበረሰቡን በፖሊሳዊ ተልዕኮ ውስጥ ማሳተፍና ራስን በዘመናዊ የወንጀል መከላከያ ስልቶች ማዘጋጀት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በጉባኤው በየክልሎች ያለውን ወቅታዊ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የተደረጉ ዝግጅቶች ላይ ውይይት ይደረጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም