አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ እሴቶች ተምሳሌት ነበሩ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ እሴቶች ተምሳሌት ነበሩ
አዲስ አበባ፤መጋቢት 29/2018 (ኢዜአ)፦አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ከፍተኛ እሴት በተግባር ያሳዩ ታላቅ ዲፕሎማት ነበሩ ሲሉ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።
ሊቀመንበሩ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ስመጥር በሆኑት አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ ህልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል።
ሊቀመንበሩ አምባሳደሯን የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ፈር ቀዳጅ፣ ታላቅ ዲፕሎማት እና ህይወታቸውን ለሀገራቸውና ለአህጉሪቱ እድገት የሰጡ ጽኑ አፍሪካዊት ሲሉ አወድሰዋቸዋል።
አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ ለበርካታ አስርተ አመታት የዘለቀ አርአያነት ያለው ሙያዊ ስኬት ማስመዝገባቸውንና ከኢትዮጵያ ቀዳሚ ሴት አምባሳደሮች አንዷ በመሆንም ለአፍሪካውያን ሴት ዲፕሎማቶች የብርሃን ፋና መሆናቸውን አመልክተዋል።
የአፍሪካን ጥቅም ለማስከበርና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር የነበራቸው የማይናወጥ ቁርጠኝነት ለአህጉራዊ የጋራ ግቦች መሳካት የጎላ ሚና እንደነበረውም አውስተዋል።
ሊቀመንበሩ አምባሳደር ቆንጂት በታማኝነት፣ በልዩ ብቃት እና ለጋራ የወደፊት እጣ ፈንታ የነበራቸው ጽኑ ቁርጠኝነት የአፍሪካ ዲፕሎማሲ እሴቶች ያላቸውን ጽኑ አቋም ያሳየ መሆኑንም ነው ያነሱት።
የአምባሳደሯ የዲፕሎማሲ አሻራ ለቀጣይ ትውልድ ዲፕሎማቶች፣በተለይም ለሴቶች፣በድፍረትና በዓላማ እንዲያገለግሉ ዘላቂ መነሳሳት ሆኖ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
ሊቀመንበሩ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ስም ለአምባሳደር ቆንጂት ቤተሰቦች፣ ለኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ፣ እንዲሁም ለሁሉም አፍሪካውያን ልባዊ መጽናናትን ተመኝተዋል።