በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተመዘገቡ ስኬቶች ከአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ጋር የተጣጣሙ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተመዘገቡ ስኬቶች ከአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ጋር የተጣጣሙ ናቸው
አዲስ አበባ፤መጋቢት 29/2018 (ኢዜአ)፦በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተመዘገቡ ስኬቶች በሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም የታቀዱና ከአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
የገንዘብ ሚኒስቴር ባለፉት 18 ወራት የተከናወኑ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ውጤታማነት የሚገመግም ዝርዝር ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ በተለይም የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ፣የወጪ ንግድን በማሳደግ እንዲሁም በመንግሥት ገቢ አሰባሰብ ላይ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡ ተመላክቷል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፤ሪፖርቱ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት እና ዓለም አቀፍ አጋሮች በጋራ ያከናወኑት የሥራ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋማዊ ቅንጅቱ ለተመዘገበው ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል።
በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተመዘገቡት ስኬቶች በሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም የታቀዱና ከአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ጋር የተጣጣሙ ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና የአገልግሎት ዘርፎችን ጨምሮ በሌሎችም ጠንካራና ሰፊ መሠረት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ እንደምትገኝ ነው የገለጹት።
ይህም የሪፎርም ፕሮግራሙ ያለመው የመዋቅራዊ ሽግግር ነጸብራቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
ባለፉት 18 ወራት ለዕድገት ዋና ምንጭ ተብለው በተለዩት አምስት የኢኮኖሚ ምሰሶዎች በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና በአይሲቲ ዘርፎች ስኬታማ ውጤቶች መመዝገባቸውን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሪፎርሙ የታሰበለትን ውጤት እያሳካ መሆኑንና የተከናወኑ ተግባራትም ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህ ስኬታማ የሪፎርም ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
ሪፖርቱ ያለፈውን ተግባር ለመገምገም ብቻ ሳይሆን የተሻለ ዕቅድ፣ የተሻለ ቅንጅት እና የተሻለ ውጤት የሚመዘገብበትን የወደፊት ጉዞ ለመቅረጽ መሠረት የሚጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
መረጃ ለተሻለ አስተዳደር መሠረት መሆኑን ጠቅሰው፥ የተጀመረው የፖሊሲ ቅንጅት እና የመረጃ መሠረተ ልማት ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡