ቀጥታ፡

የለውጡ መንግስት አሰባሳቢ ትርክትን የመገንባት ተግባር በትኩረት አከናውኗል

ወላይታ ሶዶ ፤ መጋቢት 29/2018 (ኢዜአ)፦የለውጡ መንግስት አካታች የፖለቲካ ምህዳርን በመፍጠር አሰባሳቢ ትርክትን የመገንባት ተግባርን በትኩረት ማከናወኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ አመለከቱ።

የሀገራዊ ለውጡን 8ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለተገኘው ስኬት እውቅና የሚሰጥ የድጋፍ ሰልፍ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ሶዶ ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።


 

በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ገብረመስቀል ጫላ እንደገለጹት፤ ባለፉት የለውጡ ዓመታት በሁሉም ዘርፎች ዜጎችንና ሀገሪቱን ተጠቃሚ ያደረጉ ስኬቶች ተመዝግበዋል።

መጋቢት 24 በሀገራችን ታሪክ የፖለቲካ ለውጥ የተደረገበትና አዲስ አተያይ እውን የተደረገበት ዕለት መሆኑንም ገልጸዋል።

የለውጡ መንግስት 8ተኛ ዓመትን ስናከብር በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠል ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡


 

የለውጡ መንግስት አካታች የፖለቲካ ምህዳር በመፍጠር በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ገዢ ትርክትን የመገንባት ስራ በትኩረት መስራቱንም ገልጸዋል።

ለኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶ የሆኑ ዘርፎችን በመለየት በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች መታየታቸውን የገለጹት ዋና ተጠሪው አንድነታችንን በማጠናከር የተመዘገቡ ድልና ስኬቶችን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡

የመጋቢት 24 ድል ለትውልድ ታሪክ፣ ለሀገር ደግሞ አዲስ ተስፋን የወለደ ቀን መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ ናቸው።


 

በለውጡ ዓመታት የሀገር ሉዓላዊነትን የማስጠበቅና ሀገርን የመገንባት ራዕይ እውን የሚያደርጉ ሥራዎች መሰራታቸውንም ገልጸዋል።

መጋቢት 24 አካታችና ኅብረ-ብሔራዊ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ መሠረት የተጣለበት መሆኑን ጠቅሰው በሁሉም ዘርፍ የተመዘገቡ አመርቂ ውጤቶች የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል፡፡

እንደ ዞን በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ መጋቢት 24 መንግስት ሀገርን ከመበታተን በመታደግ የለውጡ ጉዞ እንዲቀጣጠል ያደረገበት ነው ብለዋል፡፡


 

የወላይታ ሶዶ ከተማም የትሩፋቱ ተቋዳሽ በመሆኑ የአስፋልት መንገድ ግንባታ፣ የኮሪደር ልማት እና ሌሎች በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በከተማው የተጀመረውን የለውጥ ተምሳሌት ስራዎችን ለማስቀጠል የከተማ አሰተዳደሩ ከነዋሪዎች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረው ህዝቡም ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም