ቀጥታ፡

አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 29/2018 (ኢዜአ)፦አንጋፋዋ ዲፕሎማት አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

አምባሳደር ቆንጂት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በ1950ዎቹ በለጋ እድሜያቸው ተቀላቅለው ከዴስክ ኦፊሰርነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት ማገልገላቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ አመልክቷል።

አምባሳደር ቆንጂት ከዮዲት እምሩ በመቀጠል በኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ሴት አምባሳደርም ናቸው።

አምባሳደሯ በኦቶዋ፣ካይሮ፣ ቴል አቪቭና ቬይና በሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንም ቋሚ መልዕክተኛ በመሆን ሰርተዋል።

ከሰኔ 2009 እስከ መስከረም 2011ዓ.ም ደግሞ ኢጋድ በመራው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ላይም ልዩ አማካሪ ነበሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአምባሳደር ቆንጂት ሕልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ ለሟች ቤተሰቦች እና ወዳጆች መጽናናትን ተመኝቷል።

የቀብር ሽኝት ሥነ ሥርዓት መርሃ ግብሩን በቀጣይ እንደሚያሳውቅ ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም