በጠቅላላ ምርጫው የሴቶችን ተሳትፎ ማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጠቅላላ ምርጫው የሴቶችን ተሳትፎ ማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዳማ ፤ መጋቢት 29/2018 (ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን የሲቪክ ማኅበራት አስታወቁ።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ትዕግሥት ተረፈ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ፌዴሬሽኑ ለዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው።
በተለይም ሴቶች በምርጫው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።
ሴቶች የሀገሪቱን ቀጣይ አቅጣጫ በመወሰን ረገድ ያላቸውን የላቀ ሚና በመጠቀም፣ ይበጃል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ እንዲመርጡ የማንቃት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ የሚጎትቱ ችግሮችን ለመፍታትም ለቅንጅታዊ አሠራር ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።
የምርጫው በስኬት መጠናቀቅ ለሀገር ሰላምና ለዲሞክራሲ ባህል መጎልበት ያለው ሚና ወሳኝ በመሆኑ፣ ለተግባራዊነቱ ፌዴሬሽኑ በትጋት እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ፌዴሬሽን ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ እጸገነት ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ፣ ዲሞክራሲያዊና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሴቶች በንቃት እንዲሳተፉ ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሴቶች በምርጫው በመራጭነት፣ በተመራጭነትና በታዛቢነት እንዲሳተፉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የኦሮሚያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን አመራር ወይዘሮ ጀሚላ አብደላ፤ በክልሉ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች በምርጫው ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
አካል ጉዳተኞች ለሀገር ልማትና ሰላም የተሻለ አማራጭ የያዘን የፖለቲካ ፓርቲ እንዲመርጡ ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በተለይም አካል ጉዳተኛ ሴቶች በመራጭነት፣ በእጩ ተወዳዳሪነት እንዲሁም በታዛቢነት በመሳተፍ የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ምቹ ምኅዳር መፈጠሩን አድንቀዋል።