ቀጥታ፡

የአርማወር ሐንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ችግር ፈቺ የምርምርና ፈጠራ ውጤቶችን እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 29/2018 (ኢዜአ)፦የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት በሳይንሳዊ ምርምርና በፈጠራ ሥራዎች በሀገርና በአህጉር ደረጃ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአርማወር ሐንሰን የምርምር ተቋም የተገነባውንና ዘመናዊ መሠረተ ልማቶችን የያዘውን የምርምር ማዕከል መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም  መርቀው ከፍተዋል።


 

በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክትም ማዕከሉ ኢትዮጵያና አፍሪካ በሳይንሱ ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲሸጋገሩ ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።

ይህ ዘመናዊ የምርምር ማዕከል ከመሠረተ ልማት ግንባታ ባለፈ፤ በመድሃኒትና በክትባት ራሷን የቻለችና ጤናማ የሆነች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚተጋ የላቀ የዕውቀት ሥፍራ መሆኑን ተናግረዋል።

የአርማወር ሐንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተቋሙ ከሀገራዊ ለውጡ  ወዲህ በከፍተኛ አቅምና በውጤታማነት እየሠራ ነው።

ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ስምንት ዓመታት በተለይም እንደ ሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ)፣ ወባ፣ ሚኒንጃይትስና ኒሞኒያ ባሉ ተላላፊ በሽታዎች ላይ ውጤታማ ጥናቶችን ማድረጉን ጠቅሰዋል። 

ለአብነትም የሳንባ ነቀርሳ ሕክምና ጊዜን ለማሳጠር የተደረገው ምርምር ለሕዝቡ የጤና ችግር ቀጥተኛ መፍትሔ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ በዓለም አቀፍ የሳይንስ መድረክ ላይ የኢትዮጵያን አሻራ በጉልህ እያሳረፈ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 


 

በየዓመቱ ከ80 እስከ 100 የሚደርሱ የምርምር ሥራዎች በታዋቂ የሳይንስ መጽሔቶች ላይ እንዲታተሙ በማድረግ ኢትዮጵያንና አፍሪካን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በስፋት እያስተዋወቀ ነውም ብለዋል።

የተጠናቀቁና ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ ምርምሮችም በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆኑ ፕሮፌሰር አፈወርቅ አረጋግጠዋል።

ትኩረቱን ይበልጥ በማስፋት ከተላላፊ በሽታዎች በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በስፋት እየታዩ ባሉ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ ጥናቶችን እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። 

ኢንስቲትዩቱ ከጤና ዘርፍ ባለፈ ከሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር የተለያዩ የሕክምና መሣሪያዎችን በማምረት ላይ እንደሚገኝም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም