ቀጥታ፡

የወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የፖሊሲ አማራጭ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል

ጅማ፤መጋቢት 29/2018(ኢዜአ)፦የወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የፖሊሲ አማራጭ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን የጅማ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ማሳወቁ ይታወሳል።

ቦርዱ ቀደም ሲል ያወጣውን የምርጫ ካርድ የመውሰጃ ጊዜ ሰሌዳ እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ማራዘሙ ይታወሳል።

በጅማ ከተማ የሚገኙ ወጣቶች የመምረጥ መብታቸውን በመጠቀም ለሀገር ይበጃል ያሉትን ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

በምርጫው የሀገራቸውን ዕጣ ፈንታ በድምፃቸው ለመወሰን የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

ወጣቶቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የመራጭነት ካርድ በመውሰድ ለምርጫው መዘጋጀታቸው ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸውም ተናግረዋል።

ከወጣቶቹ መካከል ዲቦራ ታዬ፤ለመጀመሪያ ጊዜ ለመምረጥ ካርድ መውሰዷን ጠቅሳ የምርጫን አስፈላጊነት በመረዳት መመዝገቧን ትገልጻለች።


 

“የሀገሬን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን የኔም ድምፅ ዋጋ አለው” የምትለው ወጣቷ “ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ፓርቲ ወደ ሥልጣን እንዲመጣ ሁሉም ወጣት ድምፁን መስጠት አለበት” ስትልም ምክራለች።

ሌላው ወጣት አብዱልባሲጥ ራያ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የመራጭነት ካርድ መውሰዱ የተለየ ደስታ እንደፈጠረበት ይናገራል።


 

አብዱልባሲጥ አክሎም በወሰደው የምርጫ ካርድ የወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አካልን ለመምረጥ መወሰኑን ገልጿል።

ወደፊት ብዙ ዓላማዎች እንዳሉትና ይህንንም ለማሳካት የሚረዳውን ፓርቲ በድምፁ ወደ ሥልጣን እንደሚያመጣ ተናግሯል።

“ካርድ መውሰድ የራስን ዕድል ለመወሰን ያለውን ጠቀሜታ ትልቅ ነው” ያለው ደግሞ ወጣት ማቴዎስ ገረሹ ነው።


 

በጠቅላላ ምርጫው ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል የሚያመቻች እና የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተሰሚነት ከፍ የሚያደርግ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀቱን ገልጿል።


 

ወጣት እጅጋየሁ አስፋው በበኩሏ፣በጠቅላላ ምርጫው ሴቶችና ወጣቶች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ የሚሠራ ፓርቲን ለመምረጥ ካርዷን መውሰዷን ገልጻለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም