ኢትዮጵያ በተመድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንትነቷን በብቃት ተወጥታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በተመድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንትነቷን በብቃት ተወጥታለች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 28/2018(ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንትነቷን በብቃት መወጣቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በ61ኛ መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ፥ ኢትዮጵያ 47 አባል ሀገራት ያሉት የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል በመሆን ለሦስተኛ ጊዜ ተመርጣ በንቃት እየሠራች ትገኛለች።
በዚህ የአባልነት ዘመኗም፣ ከፌብሩዋሪ 23 እስከ ማርች 31/2026 በጄኔቫ ሲካሄድ በቆየው በ61ኛው የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ ላይ የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን የመጀመሪያውን የአመራር ኃላፊነት በብቃት ተወጥታለች ነው ያሉት።
በስብሰባው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን በሚመለከት በአባል ሀገራት የቀረቡ 38 ውሳኔዎች የተላለፉበት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም ሰባቱ ሀገር ተኮር ውሳኔዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ከሀገር ተኮር (Country Specific) ውሳኔዎች መካከል ከዩክሬን እና ሩሲያ ግጭት፣ ቤላሩስ፣ የሶሪያና ጎላን አካባቢ ባሉ ጉዳዮች፣ በፍልስጤም እና ከደቡብ ሱዳን ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ይገኙበታል ብለዋል።
በእነዚህ ሀገር ተኮር ጉዳዮች ላይ አባል ሀገራቱ ከራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም በመነሳት፥ የመደገፍና የመቃወም ውሳኔ ማሳለፋቸውን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያም እንደ አባል ሀገር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አቋሟን ማንጸባረቋን ጠቅሰው፥ ሀገራችን በመርህ ደረጃ ሀገር ተኮር ውሳኔን እንደማትደግፍ ገልጸዋል።
እንደዚህ ያሉ ውሳኔዎች ከዚህ ቀደም እንደነበሩና ኢትዮጵያ እንደምትቃወምም አንስተዋል።
ለአብነትም ኢትዮጵያ ችግር ላይ በነበረች ጊዜ ሀገራችን ባልተስማማችበት ጉዳይ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ኮሚሽን ተቋቁሞ እንደነበር አስታውሰው፥ ኢትዮጵያና ሌሎች ሀገራት በጋራ እንዲቀለበስ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
እንደዚህ ያሉ ሀገር ተኮር ጉዳዮች የሚመለከታቸው ሀገራት ሳይስማሙባቸው የሚቋቋሙ፣ የዓለም አቀፉን የወንጀል ፍርድ ቤት ሥልጣንና ሚና የሚያጣቅሱ፣ እንዲሁም የምርመራና የዓለም አቀፍ ዳኝነት ይዘት ያላቸው ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እንደዚህ ያሉ የሀገርን ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥሉ ሀገር ተኮር ውሳኔዎችን በመርህ ደረጃ እንደማትደግፍ በማንሳት፥ በጉባኤው ያሳለፈችው ውሳኔም ይህንኑ እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ፍልስጤም እና የእስራኤልን በተመለከተ በተመድ መድረክ ስታራምድ የቆየችውን አቋም አሁንም ማስቀጠሏን ገልጸዋል።
የእስራኤልና ፍልስጤም የሁለት ሀገርነት መርህን እንደምትደግፍና ከሁለቱም ጋር መልካም ግንኙነት እንዳላት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የፍልስጤምን ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እንደምትደግፍ ጠቅሰው፥ ይህንንም በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጉባኤ የተላለፈውን የፍልስጤም የራስ ገዝነት ውሳኔ (HRC/61/L.37) ደግፋ ድምፅ መስጠቷን ተናግረዋል።
የሁለት ሀገርነት መፍትሔውም በዘላቂነት በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤዎችና በጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎች መሰረት እንዲተገበር ጥሪ ማቅረቧንም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በጉባኤው በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት የአየር ትራንስፖርት፣ የመርከቦች እንቅስቃሴ፣ በቀጥታ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያሳድረውን ጫናና ስጋት ለጉባኤው መግልጿን ጠቅሰዋል።
አፋጣኝ ተኩስ አቁም እንዲደረግና መፍትሔ እንዲፈለግ ጥሪ ማቅርቧንም ተናግረዋል።