ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፈለግ የነበረ አደገኛ ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ይትባረክ ዳዊት (ክብሮም)ን ከነግብረ-አበሮቹ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ

‎አዲስ አበባ፤ መጋቢት 28 /2018 (ኢዜአ)፦ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ በማዘዋወር፣ ከ100 በላይ ሰዎችን ለሞት የዳረገ እና ከ50 በላይ ሴቶች እንዲደፈሩ ያደረገው ይትባረክ ዳዊት (ክብሮም)ን ከ9 ግብረ-አበሮቹ ጋር በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ አጠናቆ ለዓቃቢ ህግ መላኩን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኢዜአ በላከው መረጃ ይህንን ውስብስብና ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል ምርመራ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከሚሰራ The Regional Operational Centre in support of the Khartoum process (ROCK) ከተባለ ድርጅት ጋር ባደረገው የመረጃ ልውውጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፈለግ የነበረው አደገኛ ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ይትባረክ ዳዊት አለሙን በትግራይ ክልል ሽሬ ከተማ ላይ ፖሊስ በቅንጅት በቁጥጥር ሥር አውሏል።

ተጠርጣሪው በፓስፖርት ስሙ ይትባረክ ዳዊት አለሙ፣ ቤተሰቦቹ በልጅነቱ ያወጡለት ስም ጳውሎስ ዳዊት ወልዳይ፤ ወንጀል መስራት ሲጀምር የሚታወቅባቸው ስሞች አድሀኖም፣ ሱዳን ሀገር የሚታወቅበት ስም አህመድ፤ ሱማሊያ፣ ጅቡቲ እና ኬንያ የሚጠቀምበት ስም ሙኒር ሲሆን ክብሮም ደግሞ በስዊድን እና በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የሚጠቀምባቸው ሀሰተኛ ስሞች መሆናቸውን ፖሊስ በምርመራው አረጋግጧል፡፡

ፖሊስ እነዚህን ስሞች ለምርመራው አጋዥ አድርጎ ያደገ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተጠናከረ ምርመራና ክትትል በማድረግ ከ70 በላይ በሀገር ውስጥና በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ዋና ዋና የሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎችን ከለየ በኋላ ዋናውን ተጠርጣሪ ጨምሮ በአጠቃላይ 10 ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ተከታትሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራውን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ፖሊስ የተያዙትንም ሆነ ያልተያዙትን ተጠርጣሪዎች በወንጀሉ ያፈሩትን ሀብት በጥናት በመለየት ሌሎች ሀብቶቻቸውንና በባንክ የሚገኝ ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ በፍርድ ቤት እንዲታገድ ማድረጉን ገልጿል፡፡

ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪ ቡድኑ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ወጣቶችን ከኢትዮጵያ፣ ከሱዳን፣ ከኤርትራ፣ ከጅቡቲ፣ ከኬንያ እና ከሶማሊያ በመመልመል ወደ ሊቢያ በመውሰድ ሊቢያ ውስጥ ባዘጋጁት መጋዝን እንዲታገቱ በማድረግ የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ ከቤተሰቦቻቸው በማስላክ፤ ገንዘብ ያልከፈሉትን በቀን አንድ ጊዜ ብቻ በትንሹ ምግብ እንዲመገቡ በማድረግ፣ በጎማ፣ በዱላ እና በኤሌክትሪክ ገመድ በሰንሰለት እጅ እና እግራቸውን አስረው በመግረፍና በማስገረፍ፣ የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲክ አቃጥለው ሰውነታቸው ላይ በማንጠባጠብ ከፍተኛ ስቃይ በማድረስ፣ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በመፈፀም በርካታ ሰዎች ሕይወታቸው እንዲያልፍ፣ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው፣ ሴቶች እንዲደፈሩ እና ከፍተኛ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረጋቸውን ፖሊስ በምርመራ ማረጋገጥ ችሏል፡፡

ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ሊቢያ ውስጥ ተጎጅዎችን አግተው የሚያሰቃዩባቸው አምስት ማከማቻ መጋዘን እንዳላቸው እና በዚህ አደገኛ ወንጀል ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ በህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ሲንቀሳቀስ እንደነበረ ፖሊስ በሰበሰበው ማስረጃ ማረጋገጥ የቻለ ሲሆን ከ100 በላይ ተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸውን በሀገር ወስጥና በውጭ ሀገር የምስክርነት ቃል የመቀበል ሥራ መሰራቱንም ጨምሮ ገልጿል፡፡

ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሊቢያ፤ ሱዳን፤ ቤልጂየም፤ እንግሊዝ፤ ካናዳ፤ ኖርዌይ፤ ኔዘርላንድ፤ ሉግዘንበርግ እና ስዊዘርላንድ ከሚገኙ አስራ ስድስት ተጎጅዎች ላይ ቃል መቀበሉንም ፖሊስ አሳውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሀገርና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለውን ይህንን ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ለመከላከል ዘመኑ ያፈራቸውን የምርመራ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም በተሟላ ፖሊሳዊ ስብዕናና ስነ-ምግባር እየተመራ በላቀ ቁርጠኝነት ተልዕኮውን እየተወጣ ይገኛል።

ተቋሙ ከሀገራት ጋር በፈጠረው የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነትም ዓለም አቀፍ የወንጀል ተፈላጊዎችን ጭምር በቁጥጥር ሥር አውሎ በተለያየ ጊዜ ምርመራ በማጣራት በሀገር ውስጥ በህግ እንዲጠየቁና የተወሰኑት ደግሞ ከሀገራት ጋር ባለው የወንጀለኛ ልውውጥ ስምምነት መሰረት ተላልፈው እንዲሰጡ እያደረገ ይገኛል፡፡

ይህ ውስብስብ ድንበር ተሸጋሪ የወንጀል ጉዳይ በተሳካ ሁኔታ እንዲጣራ ከፖሊስ ጋር በትብብር ለሰሩት ለፍትህ ሚኒስቴር፣ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ለROCK እና በጉዳዩ ላይ መረጃ ሲሰጡ ለነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ላቅ ያለ ምስጋና እያቀረበ ኅብረተሰቡ ማንኛውንም የወንጀል ድርጊት ሲመለከት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPApp)፤ በ991 ነፃ የስልክ መስመር እና ሰው አልባ ፖሊስ ጣቢያ (SPS) በመጠቀም ወይም በአቅራቢያው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ቀርቦ ጥቆማ በመስጠት የዘወትር ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም