ቀጥታ፡

ሕገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ ተጠያቂነት ያስከትላል- የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 28/2018 (ኢዜአ)፡- ለበዓል በቂ አቅርቦት ስላለ ሕገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የበዓል የግብይት ባዛሮችን ከፍተዋል።

ሚኒስትሩ በቂርቆስና አራዳ ክፍለ ከተሞች ባዛሮችን በከፈቱበት ወቅት፤ መሰል የገበያ ትስስር መድረኮች በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞችም እንዲዘጋጁ መደረጉን ተናግረዋል።


 

በአሁኑ ወቅት በመላ ኢትዮጵያ ከ2 ሺህ 100 በላይ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ተሰናድተው ሸማቹንና አቅራቢውን በቀጥታ በማገናኘት ላይ እንደሚገኙም አረጋግጠዋል።

በባዘሮቹም የግብርናና የኢዱስትሪ ምርቶች ምክንያታዊ በሆነ ዋጋ ለሸማቹ እየቀረቡ መሆኑን አረጋግጠዋል ።

በዚህም መሠረት ለምሳሌ ቀይ ሽንኩርት በኪሎ 65 ብር፣ ድንች በኪሎ 40 ብር እንዲሁም አንድ እንቁላል በ14 ብር ሲሸጥ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በግብርና ምርቶችም ሆነ በሌሎች መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ለዋጋ ጭማሪ ምክንያት የሚሆን ምንም ዓይነት የአቅርቦት እጥረት አለመኖሩንም አስረድተዋል።


 

ከመካከለኛው ምሥራቅ ወቅታዊ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን እንደ ምክንያት በመጠቀም፣ ከነዳጅ ጋር ግንኙነት ባላቸውም ሆነ በሌላቸው ምርቶች ላይ የሚደረግ ሕገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ በምንም መልኩ ተቀባይነት እንደሌለውም አሳስበዋል ።

ነጋዴው ሕግና ሥርዓትን አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ጥሪ ያቀረቡት ሚኒስትሩ፤ ገበያውን ለመረበሽ በሚሞክሩ አካላት ላይ አስፈላጊው ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም