የመምህራን የሙያ ብቃት ምዘና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
የመምህራን የሙያ ብቃት ምዘና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ያግዛል
ደብረ ብርሃን፤ መጋቢት 28/2018 (ኢዜአ) ፡-የተጀመረው የመምህራን የሙያ ብቃት ምዘና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን እንደሚያግዝ መምህራን ገለጹ።
በአማራ ክልል በተለያዩ ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች 20 ሺህ 666 ለሚደርሱ መምህራን፣ ርእሳነ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች የሙያ ብቃት ምዘና እየተሰጠ ነውⵆ
የሙያ ብቃት ምዘናውን እየወሰዱ የሚገኙ መምህራን እንደገለፁት፤ ምዘናው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ያግዛል።
በደብረ ብርሃን ከተማ የሙያ ብቃት ምዘናውን በመውሰድ ላይ ካሉት መምህራን መካከል መምህር አጥላባቸው ለማ፤ ምዘናው የመምህራንን የሙያ ብቃት በማሻሻል ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት የሚያስችል ነው ብለዋል።
ለምዘናው የወጣው ፈተናም ከመማር ማስተማር ስነ-ዘዴ እና ከማስተማሪያ መጽሀፍት በመሆኑ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሰፊ እገዛ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት።
መምህር ተፈራ ግርማ በበኩላቸው፤ የሙያ ብቃት ምዘናው የመምህራንን አቅም ለመፈተሽ የሚያግዝ ሲሆን በቀጣይም የላቀ ክህሎትና እውቀት ባለቤት ለመሆን የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የመምህራንና የትምህርት አመራሮች የሙያ ፈቃድ አሰጣጥ እና እድሳት ባለሙያ ወይዘሮ ብዙሃን ባለው እንዳሉት፤ በክልሉ ለረጅም ጊዜ የመምህራን የሙያ በብቃት ምዘና ሳይካሄድ ቆይቷል።
በዛሬው እለትም 20 ሺህ 666 መምህራን፣ ርእሳነ መምህራንና ሱፐር ቫይዘሮች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ፈተና እየወሰዱ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘናው በክልሉ ትምህርት በሚሰጥባቸው አማርኛ፣ እንግሊዘኛ፣ አዊኛ እና ህምጥኛ ቋንቋዎች ተተርጉሞ መሆኑን አስረድተዋል
የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ የትምህርት ቤት አመራሮች የሙያ ፈቃድ አሰጣጥና እድሳት ቡድን መሪ አቶ ይልማ ጥላሁን በበኩላቸው፤ ፈተናው በመምህራን ፍላጎት ላይ ተመስርቶ መሰጠቱን ነው ያመለከቱት።
በአሁኑ ወቅትም በዞኑ በተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም በ23 ወረዳዎች 2 ሺህ 658 ባለሙያዎች ፈተናውን ለመውሰድ ችለዋል ነው ያሉት።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መቅደስ ብዙነህ በበኩላቸው፤ ምዘናው የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ ባለፈ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት የሚያስችል ነው ብለዋል።