የክልሉ ፖሊስ የፀጥታ ስጋቶችን በመለየት ወንጀል እንዳይከሰት አስቀድሞ የመከላከል ስራን በትኩረት እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ ፖሊስ የፀጥታ ስጋቶችን በመለየት ወንጀል እንዳይከሰት አስቀድሞ የመከላከል ስራን በትኩረት እያከናወነ ነው
ጎንደር፤ መጋቢት 28/2018(ኢዜአ)፡- ፖሊስ የፀጥታ ስጋቶችን በመለየት ወንጀል እንዳይከሰት አስቀድሞ የመከላከል ስራን በትኩረት እያከናወነ መሆኑን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ፡፡
ሀገራዊ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በፖሊስ ሚናና የስነ-ምግባር መርሆዎች ላይ ያተኮረ ስልጠና በጎንደር ቀጠና ለሚገኙ የፖሊስ አመራሮች እየተሰጠ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ታደሰ አያሌው ፖሊስ ወንጀልን የመከላከል ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
የክልሉ ፖሊስ በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች አማካኝነት አመራሩንና አባሉን በማብቃት የፀጥታ ስጋቶችን ቀድሞ መከላከል የሚያስችሉትን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማከናወኑንም ገልጸዋል፡፡
ፖሊስ ለህገ መንግሥቱ እና ለምርጫ ህጉ ተገዢ በመሆን መጪው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስላማዊ እንዲሆን ይሰራል ነው ያሉት።
ፖሊስ የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በማስጠበቅ ሙያዊ ኃላፊነቱ በላቀ ደረጃ እንደሚወጣም አመልክተዋል።
ፖሊስ ለምርጫው ሰላማዊነት አበክሮ ይሰራል ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አንተነህ ቴዎድሮስ ናቸው፡፡
ምርጫ ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት የሆነ የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት ማረጋገጫ ቁልፍ መሳሪያ በመሆኑ ፖሊስ ህዝባዊነቱን መሰረት በማድረግ ለምርጫው መሳካት የድርሻውን ለማበርከት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ከጎንደር ቀጠና የተውጣጡ የፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ታሳተፊ ናቸው፡፡