በክልሉ ግብርናን በማዘመን በተከናወኑ ተግባራት ምርትና ምርታማነት እያደገ መጥቷል-ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ግብርናን በማዘመን በተከናወኑ ተግባራት ምርትና ምርታማነት እያደገ መጥቷል-ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን
አሶሳ፤መጋቢት 28/2018 (ኢዜአ)፦በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርናን በማዘመን በተከናወኑ ተግባራት ምርትና ምርታማነት እያደገ መምጣቱን ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።
10ኛው ክልላዊ የግብርና ልማት አጋር አካላት የግንኙነት ካውንስል ጉባኤ፣የ2017/18 የመኸር ምርት አፈጻጸም እና የ2018/19 የመኸር ምርት ዕቅድ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እንዳሉት፥ በክልሉ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን እየተመዘገበ ያለው ለውጥ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ የኢኮኖሚ አቅሙን እንዲያሳድግ አድርጓል።
አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እየተከናወነ የሚገኘው የግብርና ሥራ ሰፋፊ ማሳዎችን በዘር ከመሸፈን ባለፈ ምርታማነት እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል።
በክልሉ በሌማት ትሩፋት፣በአረንጓዴ አሻራ፣በሩዝ፣ በስንዴና በተፋሰስ ልማት እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች ተግባራትን በማጠናከር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት ያከናወናቸው የመስኖ ግንባታዎች እና ዘርፉን የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ሀሊፋ በበኩላቸው፤ በ2017/18 የመኸር እርሻ 55 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን አስታውቀዋል።
በ2018/2019 የመኸር እርሻ በክልሉ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በማልማት ከ70 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ለማግኘት ዕቅድ መያዙን ኃላፊው ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዘርፉ አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።