ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር ያላትን ወዳጅነት ይበልጥ ለማሳደግ በቁርጠኝነት ትሰራለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር ያላትን ወዳጅነት ይበልጥ ለማሳደግ በቁርጠኝነት ትሰራለች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 28/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር ያላትን ታሪካዊና ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት እንደምትሰራ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ በኢትዮጵያ የኳታር መንግስት አምባሳደር ሰአድ ሙባረክ አል-ናይሚ ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ውይይቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ታሪካዊና ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።
ሁለቱ አመራሮች በቆይታቸው በኢንቨስትመንት መስፋፋት እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በሚሰሩ የልማት ስራዎች ዙሪያ በዝርዝር መክረዋል።
በተለይም የኳታሩ ሹራ ካውንስል (Shura Council) ከብልፅግና ፓርቲ እና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚችልባቸው መንገዶች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
አቶ አደም ፋራህ በብልፅግና ፓርቲ መሪነት በኢትዮጵያ እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ-ብዙ የልማት ስራዎችንና እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን ለአምባሳደሩ አብራርተዋል።
በተለይም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት፣ የግብርና ምርታማነት እና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሮች የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ያላቸውን ጉልህ ሚና በዝርዝር አንስተዋል።
አምባሳደር ሰአድ ሙባረክ አል-ናይሚ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ዘርፎች እየተመዘገበ ያለው ውጤት አመርቂ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም ሀገሪቱ ተግባራዊ ያደረገችውን የተሟላ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ ተገማች፣ ግልጽና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ መፈጠሩን አመልክተዋል።
አምባሳደሩ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተገኝተው ባደረጉት ምልከታ የልማት ስራዎች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን መታዘባቸውንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም አቶ አደም ፋራህ በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እንዲሆን ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ለአምባሳደሩ ገልጸውላቸዋል።
ኢትዮጵያ ለሰፊ ኢንቨስትመንትና ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ያላትን ቁርጠኝነትም በዚሁ ወቅት አረጋግጠዋል።
የኳታር መንግስት በተለያዩ ዘርፎች ለኢትዮጵያ እያደረገ ስላለው ድጋፍ አቶ አደም ፋራህ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ከኳታር ጋር ያላትን ወዳጅነት ይበልጥ በማሳደግ ለሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትና ለቀጣናዊ መረጋጋት በቁርጠኝነት መስራቷን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።