ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን አቀናጅቶ በመምራት ዘርፈ ብዙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን አቀናጅቶ በመምራት ዘርፈ ብዙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ሀዋሳ ፤መጋቢት 28/2018 (ኢዜአ)፡- ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን አቀናጅቶ በመምራት ዘርፈ ብዙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ዘሃራ ሁመድ ገለጹ።
የደቡብ ኢትዮጵያና አጎራባች ክልሎች የመንግስታት ግንኙነት መድረክ በሃዋሳ እየተካሄደ ነው።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ዘሃራ ሁመድ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በጠበቀና አቀናጅቶ በመምራት ዘርፈ ብዙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ተከናውነዋል ።
በመሆኑም መደበኛ የመንግስታት ግንኙነቶችን ለማጠናከር የሚረዳ የመንግስታት ግንኙነት ስርዓት አዋጅ ተደንግጎ እየተሰራበት ነው ብለዋል።
የመንግስታት ግንኙነት ስርዓት የህዝቦችን ግንኙነትና ትስስር በማጠናከር በመንግስታት መካከል ያሉ የጋራ ግንኙነቶችን በአጋርነትና በትብብር ለመስራት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ተቋማዊ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ጤናማ የፌደራል ስርዓት ለመገንባት፣ ህገ-መንግስታዊ መሰረትን ለማስፋትና ለማጠናከር እንዲሁም ቀጣይነቱን ለማስጠበቅ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
በምክር ቤቱ የመንግስታት ግንኙነት፣ የዲሞክራሲያዊ አንድነትና የሕገ መንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ወይዘሮ ባንቺይርጋ መለሰ በበኩላቸው ተቋማቱ የተረጋገጠ የርስ በርስ ግንኙነቶችን በማጎልበት የጋራ ልማትን የሚያጠናክሩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የዛሬው መድረክ ዋና ዓላማም ከዚህ ቀደም በተደረጉ መድረኮች የተገኙ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠልና ክፍተቶችን በመሙላት የመንግስታትና የህዝቦችን ግንኙነትን ለማጠናከር መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በመርህ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የትብብር ስርዓት በማጎልበት ለፌደራላዊ ስርዓቱ ይበልጥ መጠናከር ክልሎች የድርሻቸውን እንዲወጡ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት የመንግስታትን ግንኙነት በማጠናከር በተከናወኑ ተግባራት ዘርፈ ብዙ ውጤቶች መገኘታቸውን የገለጹት ደግሞ የሲዳማ ክልል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ ናቸው።
የዘንድሮ የግንኙነት መድረክም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በተቃረበ ጊዜ የሚካሄድ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
"የትብብር ፌዴራሊዝም ሞዴል እና የመንግስታት ግንኙነት በህብረ-ብሔራዊ ፌደራል ስርዓት፣ የኢትዮጵያ ሁኔታ" በሚል ርእስ በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።
በመድረኩም አፈ-ጉባኤዎች፣ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች፣ የህግ አማካሪዎችና የፍትህ ቢሮ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።