ቀጥታ፡

በምዕራብ ወለጋ ዞን ከ119 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እየቀረበ ነው

ጊምቢ፣ መጋቢት 28/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ከ119 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑን የዞኑ የኅብረት ሥራ ማህበራት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የዞኑ ኅብረት ሥራ ማህበራት ጽሕፈት ቤት የምርት ግብዓትና አቅርቦት ቡድን መሪ አቶ ተሰፋዬ ታሲሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለ2018/19 የምርት ዘመን የመኸር እርሻ 235 ሺህ 572 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ እየተሰራ ይገኛል።

እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ 119 ሺህ 731 ኩንታል ማዳበሪያ በዞኑ መድረሱን ገልጸው ከደረሰው ውስጥ 18 ሺህ 849 ኩንታል በላይ የሚሆነው ለአርሶ አደሩ ጋር ደርሷል ብለዋል።


 

ስርጭቱ በዞኑ በሚገኙ አራት ዩኒየኖችና በየደረጃው ባሉ የኅብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት እየተከናወነ መሆኑ ጠቁመዋል።

የዘንድሮው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት በወቅቱ መከናወኑን የገለጹት ቡድን መሪው፤ የአቅርቦት ሂደቱም ካለፉት ጊዜያት በተሻለ ሁኔታ ለአርሶ አደሩ እንዲከፋፈል እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የላሎ አሳቢ ወረዳ አርሶ አደር ኦላኒ ሀብታሙ፤ ለዘንድሮ የእርሻ ሥራ የሚውል ማዳበሪያ በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ለማድረስ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ገልጸዋል። 

ይህም የእርሻ ሥራቸውን በተሟላ ዝግጅት ለማከናወን እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

የጊምቢ ወረዳ አርሶ አደር ቡልቲ ኑሩ በበኩላቸው፤ ማዳበሪያው በኅብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት በጊዜ መሰራጨቱ አሁን ያለውን ዝናብ በመጠቀም የመሬት ዝግጅት ሥራቸውን አስቀድመው እንዲያጠናቅቁና የተሻለ ምርት እንዲያገኙ እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኢ- ተገማችና ተለዋዋጭ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ ቀደም ብላ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ በመፈጸም ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቷን የግብርና ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም