ቀጥታ፡

የለውጡ ዓመታት በሁሉም ዘርፎች ትልልቅ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው- ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

ቦንጋ፤ መጋቢት 28/2018(ኢዜአ)፦ የለውጡ ዓመታት በሁሉም ዘርፎች ትልልቅ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ እውን የሆነበትን 8ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል ።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፤ መጋቢት 24/2010 ዓ.ም የዴሞክራሲ መሰረት የተቀመጠበትና የመደመር እሳቤ የተበሰረበት ታሪካዊ እለት መሆኑን ገልጸዋል።

የለውጡ ሂደት የተለያዩ ፈተናዎች ያጋጠሙት ቢሆንም ችግሮችን ወደ አድል በመቀየር በሁሉም ዘርፎች ትልልቅ ስኬቶች የተመዘገቡበት መሆኑን ተናግረዋል።

በብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፎች በመመራት የህዝብን ተጠቃሚነት እውን ማድርግና ምርታማነትን ማሳደግ የተቻለበት መሆኑን ገልጸዋል። 

በከተሞችም ይሁን በገጠር የቆዩ የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ምላሽ በመስጠት እድገትና ማንሰራራት እውን እንዲሆን የተሰራበት ስኬታማ የለውጥ አመታት መሆኑን አንስተዋል።


 

የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እንዳሻው ከበደ፤ በለውጡ ዓመታት እንደ ሀገር የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎችም ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅና ሌሎችንም መጀመር መቻሉ በቀጣይ ትልቅ ሀገራዊ ተስፋ የሰነቀ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በለውጡ ዓመታት የተመዘገቡ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ይበልጥ መትጋት ይኖረብናል ብለዋል። 

የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተክለአብ ቡሎ (ዶ/ር)፤ በለውጡ ዓመታት በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶች የተገኙት በህዝቡ ጠንካራ ትብብር መሆኑን አንስተው ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንሰራለን ብለዋል።


 

በድጋፍ ሰልፉ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ በዞኑ ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም