በአፍሪካ ለአደጋ ስጋት ምላሽ አህጉራዊ አቅምን ማጠናከር ላይ ያተኮረ ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ለአደጋ ስጋት ምላሽ አህጉራዊ አቅምን ማጠናከር ላይ ያተኮረ ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 28/2018 (ኢዜአ) ፦ 16ኛው የአፍሪካ አደጋ ሥጋት አቅም አህጉራዊ ጉባኤ ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 1 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ገለጹ።
ኮሚሽነሩ ጉባኤውን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት፤ ጉባኤው በዋናነት በአፍሪካ አህጉር የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከልና የአደጋ ሥጋት ፋይናንስ አቅምን ለማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ይመክራል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ፣ በምግብ ሉዓላዊነት፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ እንዲሁም በሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነት ላይ ያከናወነቻቸው ስኬታማ ተግባራት በመሪነት እንዲታይ በማድረጋቸው፣ ጉባኤውን እንድታስተናግድ መመረጧንም አስታውሰዋል።
በዚሁ ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችን ጨምሮ 300 ተሳታፊዎች ይታደማሉ ።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ አደጋዎች ቢጨምሩም፣ ዓለም አቀፍ አጋርነትና ድጋፍ ግን እየቀነሰ መምጣቱን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
አፍሪካ ለችግሮቿ የራሷን መፍትሄ ለማበጀት በራሷ የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና የሀብት አቅም የሚመራ ተቋም እንደሚያስፈልጋትም ገልጸዋል።
በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ሥር የሚገኘው የአፍሪካ አደጋ ሥጋት አቅም ቡድን ለዚህ ተጠቃሽ ተቋም መሆኑን አብራርተዋል።
በቀጣይ ቀናት የሚካሄደው አህጉራዊ ጉባኤ አፍሪካ መር የአደጋ ስጋት ምላሽ አቅምን ማጠናከር ላይ በስፋት እንደሚመክር ጠቁመዋል።
የውጭ እርዳታ ጥገኝነት አስተሳሰብን መለወጥ፤ በፋይናንስ አቅም ላይ የአባል ሀገራትን መዋጮ ማሳደግ፤ ተቋማዊ ቁመናን በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ማጠናከር ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ አብራርተዋል።
በጉባኤው ላይ የሚሳተፉ እንግዶች በቆይታቸው በከተማዋ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች፣ ብሔራዊ ቤተ-መንግሥትና ሌሎች ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን እንደሚጎበኙም ይጠበቃል።