ቀጥታ፡

መጋቢት 24 ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ለማሸጋገር የለውጥ ንጋት የፈነጠቀበት ታላቅ ዕለት ነው - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ሐረር፤ መጋቢት 28/2018(ኢዜአ) ፦ መጋቢት 24 ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ለማሸጋገር የለውጥ ንጋት የፈነጠቀበት ታላቅ ዕለት ነው ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።

በለውጡ የተገኙ ድሎችና ስኬቶችን ለማስቀጠል ያለመ ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ በሐረር ከተማ ተካሂዷል።

በዚሁ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ በክልሉ ከገጠርና ከከተማ የተውጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎችም ተሳታፊ ሆነዋል።


 

በኢማም አህመድ ስታድየም ለድጋፉ ለተገኘው ህዝብ ንግግር ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ባለፉት 8 የለውጥ ዓመታት ታላላቅ ሀገራዊና ክልላዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል።

እለቱ በተለያዩ የልማት መስኮች ድል ለማስመዝገብ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዚህም ህብረ ብሔራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት የተፈጠረበት ሀገረ መንግስት በመገንባት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የለውጡ ዓመታት ጠንካራ የአመራር ውህደት የተፈጠረበትና ከፍተኛ የልማት መነሳሳት የታየበት መሆኑን ገልጸው፤ የህዝብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ነው ብለዋል።

በዚህም የለውጡ መንግስት ሀገር መምራት ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች እመርታዎች መመዝገባቸውንም አመልክተዋል።

አገሪቷ የጀመረችውን ሁሉ አቀፍ የልማት ስራዎችን ህዝቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ከመንግስት ጎን በመሆን እያከናወነ የሚገኘውን ተግባር ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ ለመራጭነት የሚያበቃውን የምርጫ ካርድ በመውሰድ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባም ጥሪ አስተላልፈዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ በበኩላቸው የለውጡ መሐንዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ አመራር የመጡበት መጋቢት 24 በታሪክ አጋጣሚ የተከሰተ ሳይሆን በሕዝብ ትግልና መስዋዕትነት የመጣ የድል ፍሬ ነው ብለዋል።

መጋቢት 24 በሀገራችን ኢትዮጵያ የዘመናት ጭቆናና ኢ-ፍትሃዊ ስርዓት ከህዝባችን ጫንቃ ላይ የተነሳበት፤ በአዲስ አስተሳሰብና በአዲስ እይታ አካታች፣ ህብረ ብሄራዊ፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነት የተጠናከረበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

አቶ ጌቱ አክለውም እለቱ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማዕከል ያደረገ የመደመር መንግስት የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት የሀገረ መንግስት ግንባታ በይፋ የተጀመረበት ታሪካዊ ቀን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም