ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ከ20 ሺህ ለሚበልጡ መምህራን እና የትምህርት አመራሮች የሙያ ፍቃድ ምዘና እየተሰጠ ነው

ደሴ፤  መጋቢት 28/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ከ20 ሺህ ለሚበልጡ መምህራን እና የትምህርት አመራሮች የሙያ ፍቃድ ምዘና እየተሰጠ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ደምስ እንድሪስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ለመምህራንና ለትምህርት አመራሮች እየተሰጠ ያለው የሙያ ፍቃድ ምዘና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

በተጨማሪም የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል፣ የመምህራንንና የትምህርት አመራሩን ብቃት ለማሳደግ እና ስነ- ምግባርን ለማሻሻልም ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

በዛሬው እለትም በክልሉ በ535 ምዘና ማዕከላት ከ20 ሺህ 400 የሚበልጡ መምህራንና የትምህርት አመራሮች  የሙያ መመዘኛ ፈተናውን እየወሰዱ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በምዘናው ወቅት መምህራንና አመራሮቹ ላይ ያታዩትን ክፍተቶች በመለየት የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥም ነው አቶ ደምስ የተናገሩት።

በምዘናው የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡት ደግሞ የሙያ ፍቃድ ከማገኘት ባለፈ የደረጃ እድገት ሲኖር ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችልም ነው የጠቀሱት።

በየዓመቱ ተመሳሳይ ምዘና የሚካሔድ ሲሆን በዘንድሮው ምዘና ያለተካተቱ በቀጣይ አመት እድሉ እንደሚኖር ነው ያብራሩት።

ምዘናው በሁሉም አካባቢዎች በስኬት እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው ለአስተባባሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።

የዘንድሮው የመማር መስተማር ሥራ በተሻለ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተማሪዎች በ12ኛ፣ 8ኛ እና 6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡም ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም