ቀጥታ፡

የክልሉን ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ ለማድረግ የጸጥታ ሀይሉ የህግ ማስከበር ተግባሩን በላቀ ሁኔታ እየተወጣ ነው

ባህርዳር፤ መጋቢት 28/2018 (ኢዜአ) ፦ በአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታን አስተማማኝ ለማድረግ የጸጥታ ሀይሉ የህግ ማስከበር ተግባሩን በላቀ ሁኔታ እየተወጣ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለፁ።

የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በየደረጃው ለሚገኙ የፖሊስ አመራሮች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖሊስ አባላት ሚና እና ስነ-ምግባር ላይ በማተኮር የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ማካሔድ ጀምሯል።


 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ እንደሆነ ይታወቃል።

የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) እንዳሉት የክልሉን ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ ለማድረግ የጸጥታ ሀይሉ የህግ ማስከበር ተግባሩን በላቀ ሁኔታ እየተወጣ መሆኑንም አስረድተዋል።

ህዝብ በመረጠው መንግስት መመራት እንዲችል ምርጫ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው የሰለጠነ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫ መሆኑንም አንስተዋል።

ይህን እውን ለማድረግም ፖሊስ ገለልተኛነቱን በጠበቀ አግባብ ምርጫው ያለ ምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወን እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የፀጥታ ሀይሉ የምርጫ ሂደቱን ስኬታማ ማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ምርጫውን በተጀመረው አግባብ በስኬት ለማከናወን በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ከፀጥታ ሀይሉ ጎን በመሆን እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ስልጠናው ባህርዳርን ጨምሮ በስድስት ማዕከላት የተጀመረ ሲሆን በምርጫ ዙሪያ በተዘጋጁ ሰነዶች እየተሰጠም ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም