ቀጥታ፡

በክልሉ በመደመር እሳቤ በመመራት የተመዘገቡ ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ሚዛን አማን፤ መጋቢት 28/ 2018 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በመደመር እሳቤ በመመራት የተመዘገቡ ውጤቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን ገለጹ። 

የለውጡን ስምንተኛ ዓመት የሚዘክር የድጋፍ ሰልፍ በሚዛን አማን ከተማ የተካሄደ ሲሆን በዕለቱም የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።   


 

በድጋፍ ሰልፉ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ፍቅሬ አማን፤ የለውጡ ትሩፋት የሆነው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከተመሰረተ በኋላ በክልሉ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች መምጣታቸውን ገልጸዋል።   

በመደመር እሳቤ እየተተገበሩ ያሉ ፕሮጀክቶችን በማጠናከር የሕዝብ ተጠቃሚነትን ይበልጥ ከፍ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።   

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የመጡ ውጤቶችን በማስፋት፣ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሕዝቡ ተሳትፎ ጉልህ መሆኑን ጠቁመዋል።   

የኮሪደር ልማት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና የገጠር ትራንስፎርሜሽን ተግባራት የዕድገት ጉዞው ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሕዝቡ ለሀገር ልዕልና በጋራ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።   

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በበኩላቸው፤ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የተስፋ መነሻና የብልጽግና ጉዞ መሠረት የተጣለበት ታሪካዊ ቀን መሆኑን ገልጸዋል።   


 

በለውጡ ዓመታት መንግሥት ያለፉ ስብራቶችን እየጠገነ መምጣቱን የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ ሕዝብን ባሳተፈ ተግባር የተመዘገቡ ውጤቶች የዞኑን ተጠቃሚነት ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።   

በተለይም የዞኑን እምቅ የተፈጥሮ ጸጋዎች ወደ ተጨባጭ ልማት የመቀየር ሥራ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አክለዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተሳተፉት አቶ አማኑኤል ዘለቀ፤ በከተማዋ እየታዩ ያሉ የልማት ውጤቶች የለውጡ ፍሬዎች መሆናቸውን ገልጸው፣ ለተጨማሪ ስኬት ከመንግሥት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።   


 

ሌላዋ የሰልፉ ታዳሚ ወይዘሮ ሚሚ ወልደሰንበት በበኩላቸው፤ ባለፉት ስምንት ዓመታት የተከናወኑ ሥራዎች ውጤታቸው ከሚጠበቀው በላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ላይ አሻራቸውን ለማሳረፍ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።


 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም