ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ለመጪው የትንሣዔ በዓል የሚሆን በቂ የፍጆታ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ ነው- ንግድ ቢሮ

አዲስ አበባ ፤መጋቢት 28/2018(ኢዜአ)፡- በመዲናዋ ለመጪው የትንሣዔ በዓል የሚሆን በቂ የፍጆታ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ ገለጹ።

የቢሮ ኃላፊዋ የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተከናወኑ የገበያ ማረጋጋት ስራዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ ተገቢ ያልሆነ  የምርቶች የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር ለመከላከል በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በተለይ ደግሞ ከተለያዩ ክልሎች ጋር በመተሳሰር የግብርና እና የኢንዱስትሪ የፍጆታ ምርቶች በጥራትና በስፋት ወደ ከተማዋ እንዲገቡ  እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማዋ በሚገኙ ስድስት የገበያ ማዕከላት፣ በሰንበት ገበያዎች፣ በሸማች ማህበራት እና በንግድ ስራ ድርጅት በቂ ምርት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ ነው ብለዋል።

እንዲሁም በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ዛሬ ከሰዓት ጀምሮ  ምርቶች ለግብይት የሚቀርቡበት ባዛር እንደሚከፈት ተናግረዋል።

የጤፍ፣ የሽንኩርት፣ የዘይት ፣የእርድ እንስሳት እና ሌሎች የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በስፋት እየቀረቡ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ህብረተሰቡ ክፍሎችን የመግዛት አቅም ታሳቢ በማድረግ እንዲቀርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በቀጣይም በዓሉን ምክንያት በማድረግ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ጠንካራና ጥብቅ የክትትል እና ቁጥጥር ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም