ቀጥታ፡

በጠቅላላ ምርጫው ለሀገር የሚበጅ የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የመራጭነት ካርድ ወስደናል- የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች

አምቦ፣ መጋቢት 28/2018 (ኢዜአ)፦ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫው ሀገርን የሚያሻግር ሀሳብ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።   

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ማሳወቁ ይታወሳል።   

ቦርዱ ቀደም ሲል ያወጣውን የምርጫ ካርድ የመውሰጃ ጊዜ ሰሌዳ እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ማራዘሙ ይታወሳል።   

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች፤ ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም፣ ለሀገር ሰላምና ልማት መቀጠል የተሻለ ሀሳብ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ መውሰዳቸውንና በተለያዩ መንገዶች የሚደረጉ የምርጫ ክርክሮችን እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።   


 

ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ ኦልአንቱ ባንቲ በምርጫው የሴቶች እኩልነትና ነፃነትን ለማስከበር የሚሰራ የፖለቲካ ፓርቲን ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ ወስደዋል። 

ኢትዮጵያን ወደተሻለ ምዕራፍ ያሸጋግራል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫውን ዕለት በጉጉት እየጠበቁ መሆኑንም ተናግረዋል።   

በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ለሀገራዊ እድገት የበኩላቸውን ለመወጣት የሚያበቃቸውን የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው ነዋሪ አቶ አበበ በቃና ናቸው። 

እንደ ሀገር የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል ሁሉም ሰው በተሰጠው ተጨማሪ ቀን የመራጭነት ካርዱን እንዲወስድም ከልምዳቸው መክረዋል።   

ዲሞክራሲያዊና የበለጸገች ሀገርን ለመገንባት በምርጫ ሂደት መሳተፍ የዜግነት ግዴታ ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሳራ ማሞ ናቸው። 

በምርጫው ሰላማዊና ፍትሐዊ እንዲሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡና ለዚህም የምርጫ ካርድ በመውሰድ የፈለጉትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም