በክልሉ የ12ኛ ክፍል የ'ኦንላይን' ፈተና አሰጣጥ ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የ12ኛ ክፍል የ'ኦንላይን' ፈተና አሰጣጥ ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው
አዲስ አበባ ፤መጋቢት 28/2018(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የ'ኦንላይን' ፈተና አሰጣጥ ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ካሳሁን ገላና (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ በወረቀትና በ'ኦንላይን' ሲሰጥ የነበረውን ፈተና ዘንድሮ በ'ኦንላይን' ለመፈተን መታቀዱን ገልጸዋል።
በዚህም በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በክልሉ ብሔራዊ ፈተናውን የሚወስዱ 180 ሺህ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በ'ኦንላይን' እንዲፈተኑ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።
እስካሁን ባለው ሂደትም ከ180 በላይ የፈተና ጣቢያዎች ተለይተው የተቋቋሙ ሲሆን፤ በቀሪ ወረዳዎችና ዞኖችም የፈተና ጣቢያዎችን የማደራጀት ሥራው ቀጥሏል ብለዋል።
በፈተና ጣቢያዎቹ ተጨማሪ ኮምፒውተሮችን የማሟላትና የኢንተርኔት መሰረተ ልማት ዝርጋታም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ተፈታኝ ተማሪዎች ከ'ሲስተሙ' ጋር እንዲላመዱ የሙከራ ፈተናዎች በ'ኦንላይን' እየተሰጣቸው ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ምክትል ኃላፊው አክለዋል።
ፈተናው በየወረዳው በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።
የ'ኦንላይን' ፈተናው ዘመናዊና ውጤታማ ከመሆኑም ባለፈ ተማሪዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ሳይርቁ በአቅራቢያቸው በሚገኙ ጣቢያዎች በተረጋጋ ስሜት ለፈተና እንዲቀመጡ እንደሚረዳቸውም አመልክተዋል።
በተጨማሪም የ'ኦንላይን' ፈተናው "ዲጂታል 2030" እቅድን እውን ለማድረግና የዲጂታል ትምህርትን ለማስፋፋት ትልቅ መሰረት እንደሚጥልም አመልክተዋል።