ቀጥታ፡

ለመዲናዋ ነዋሪዎች የገባነውን ቃል በተግባር በመፈጸም ተጠቃሚነትን እናረጋግጣለን - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2018(ኢዜአ)፦ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የገባነውን ቃል በተግባር በመፈጸም ተጠቃሚነትን እናረጋግጣለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የአዲስ ስፖርት ፓርክን ትናንት መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም መርቀው ለህዝብ ክፍት ማድረጋቸው ይታወቃል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ ስፖርት ፓርክ ግንባታ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋና እና የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር አካሂዷል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ አዲስ ስፖርት ፓርክ ሁሉንም የስፖርት ዓይነቶች ማዘውተር የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች የተሟሉለትና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘመናዊ ፓርክ ነው።




ፓርኩ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ያስጠሩ ዝነኛ አትሌቶች በክብር ታስበው እውቅና ያገኙበት ልዩ ስፍራ መሆኑን በመጥቀስ፤ በዘርፉ አዳዲስ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች በማነቃቃት ብቁ ተተኪዎችን ለማፍራት ታስቦ የተገነባ መሆኑንም አብራርተዋል።

ይህ ዘመናዊ ፓርክ ከመዲናዋ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ጋር የተሳሰረ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአዲስ ዕሳቤ የተገነባ ትልቅ የልማት ፍሬ መሆኑን ገልጸዋል።

አስተዳደሩ የገባውን ቃል በተግባር በመፈጸም ጥራት ያላቸውንና ዜጎችን በላቀ ደረጃ የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶችን ለህዝብ ተደራሽ የማድረግ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ከንቲባዋ ለአዲስ ስፖርት ፓርክ ግንባታ መሳካት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የአዲስ ስፖርት ፓርክ በአምስት ነጥብ ሰባት ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ ከመዲናዋ የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክት ጋር ተሰናስሎ የተገነባ የስፖርት ማዕከል ነው።

በአዲስ አበባ ዑራኤል አካባቢ በተገነባው ፓርክም በዓለም የኦሎምፒክ መድረክ የኢትዮጵያን ስምና ዝና ከፍ በማድረግ የወርቅ ሜዳልያ ያስገኙ 15 ጀግና የአትሌቲክስ ፈርጦችን የሚዘክር ሐውልት ቆሟል።

በስፖርት ማዕከሉ ለተተኪ ትውልድ በትዕምርትነት የሚያገለግል ዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ደረጃን ያሟሉ ዘመናዊ የመዋኛ ገንዳ፣ የእግር እና የቅርጫት ኳስ፣ የቴኒስና የሩጫ ትራክንና ሜዳዎችን አካትቷል።

በተመሳሳይም በአንድ ጊዜ እስከ ሦስት ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ሰፊ ፕላዛ እና በአንድ ጊዜ 300 መኪናዎችን ማስተናገድ የሚችል ባለ ሁለት ወለል የምድር ቤት ተሽከርካሪ ማቆሚያም አካቷል።

በልማት ምክንያት ለሚነሱ ዜጎች አቅም የሚያጎለብቱ አዳዲስ የንግድ ሱቆችም የፓርኩ ግንባታ አካል ናቸው።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም