የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት የሚያስቀጥል የፖሊሲ አማራጭ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ ወስደናል -ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት የሚያስቀጥል የፖሊሲ አማራጭ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ ወስደናል -ወጣቶች
ጭሮ፤መጋቢት 27/2018 (ኢዜአ)፡-በጠቅላላ ምርጫው የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እድገት የሚያስቀጥል የፖሊሲ አማራጭ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የሂርና ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
የምርጫ ካርድ ያልወሰዱ ቀነ ገደቡ ሳይጠናቀቅ በመራጭነት ተመዝግበው ካርድ እንዲወስዱ ወጣቶቹ ጥሪ አቅርበዋል።
የምርጫ ሂደቱን አስመልክተው የሂርና ከተማ ወጣቶች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንደ ሀገር የተገኙ ልማቶችን አጠናክሮ የሚያስቀጥል የፖሊሲ አማራጭ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ ወስደዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ ወጣቶች መካከል ወጣት ያሲን አህመዲን እንዳለው በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት እየተሳተፈ ነው።
በሀገሪቱ የተጀመሩ ሁሉን አቀፍ ልማቶችን ለማስቀጠልና ዴሞክራሲያዊ ስርአት እንዲጠናከር በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ለማበርከት የምርጫ ካርድ መውሰዱን ተናግሯል።
ሌሎችም የምርጫ ካርድ በመውሰድ የዜግነት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ መክሯል።
ወጣቶች በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ ለዲሞክራሲ ግንባታና ለሀገር እድገት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ የጠየቀው ደግሞ ወጣት ዝያድ ያሲን ነው።
ለምርጫው ፍትሀዊነትና ሰላማዊነት የወጣቶች ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ለመምረጥ የሚያስችለውን ካርድ በወቅቱ መውሰዱን ተናግሯል።
የመራጭነት ካርድ ያልወሰዱ ወጣቶች የመራጮች ምዝገባ ጊዜ ሳይጠናቀቅ ተመዝግበው ካርድ እንዲወስዱ መክሯል።
ሌላኛዋ የከተማው ነዋሪ ወጣት ሮዛ ያሲን በበኩሏ የበለፀገች ሀገር ለመገንባት በምርጫ በንቃት መሳተፍ ወሳኝ መሆኑን አስረድታለች።
በገጠርና ከተሞች እየተስተዋለ ያለው ፈጣን ልማት ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረጉን ገልፃ ልማቱን ለማስቀጠል ይበጃል የምትለውን ፓርቲ ለመምረጥ ከወዲሁ የምርጫ ካርድ ወስጃለሁ ነው ያለችው።
ለመራጮች ምዝገባ የተቀመጠው ቀነ ገደብ ሳይጠናቀቅ ህብረተሰቡ የምርጫ ካርድ እንዲውስድ ወጣቶቹ መልዕክት አስተላልፈዋል።