ለምርጫው ሂደት ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊነት የበኩላችንን ሚና እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
ለምርጫው ሂደት ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊነት የበኩላችንን ሚና እንወጣለን
አዲስ አበባ፤መጋቢት 27/2018 (ኢዜአ)፦በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ ለምርጫው ሂደት ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊነት የበኩላችንን ሚና እንወጣለን ሲሉ ወጣቶች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መርሃ ግብር መሰረት የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል፤ የመራጮች ምዝገባም እየተከናወነ ይገኛል።
በምርጫው ከ23 ሺህ በላይ ወጣቶች በምርጫ ታዛቢነት እንደሚሳተፉ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አሌክሳንደር ንጉሥ ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቆይታ እንደገለጸው፤ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና አካታች እንዲሆን ፌዴሬሽኑ የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያከናውን ቆይቷል።
በዚህም መሠረት ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡና በፌዴሬሽኑ ሥር የሚገኙ ከ23 ሺህ በላይ ወጣቶች በታዛቢነት ተመዝግበው ለሥራ መዘጋጀታቸውን አረጋግጧል።
ምርጫ ለአገር ዕድገትና ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማይተካ ሚና እንዳለው የገለጸው ወጣት አሌክሳንደር፤ ወጣቶችን በሀገሪቷ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለመጻኢ ዕድላቸው መሠረት ሊጥሉ ይገባል ነው ያለው።
በተለይም የሥልጣን ሽግግር በምርጫና በምርጫ ብቻ ሊሆን እንደሚገባ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እንደተከናወነም ነው የገለጸው።
የነገዋን ኢትዮጵያ የመረከብ ኃላፊነት ያለባቸው ወጣቶች፣ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው በምርጫው ወቅት የሚጠበቅባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል።
ወጣቶች የነገዋን ኢትዮጵያ መገንባትና ማስቀጠል ላይ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልፆ፤ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በምርጫ በንቃት ሊሳተፉ እንደሚገባ ተናግሯል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች በበኩላቸው፣ በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ወጣት ሩት ሸዋንቅጣው እንደምትናገረው፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በመሳተፍ ዲሞክራሲያዊ መብቷን ለመጠቀም ተዘጋጅታለች።
በምርጫው ከመሳተፍ ባለፈ የሌሎችን ግንዛቤ ለማሳደግ እንደምትሰራ የገለፀችው ደግሞ ወጣት ቢታንያ አለምሰገድ ነች።
ወጣት ናታኔም ፀጋ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት የሚያስችል በመሆኑ ወጣቶች በንቃት ልንሳተፍ ይገባል ብላለች።
የምርጫው ሂደት ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም ወጣቶቹ አረጋግጠዋል፡፡