ቀጥታ፡

ውድድሩ ህብረ ብሄራዊ አንድነትና ሀገራዊ መስተጋብርን በአንድ መድረክ ያሳየ ነው

ሐረር፤መጋቢት 27/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህልና ስፖርቶች ውድድር ህብረ ብሄራዊ አንድነትና ሀገራዊ መስተጋብርን በአንድ መድረክ ያሳየ መሆኑን የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ህይወት መሀመድ ገለጹ፡፡

"የባህል ስፖርቶች ልማት ለኢትዮጵያ ከፍታ'' በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 20 እስከ 27 በሐረሪ ክልል ሲካሄድ የነበረው 23ኛው የኢትዮጵያ የባህልና ስፖርቶች ውድድር እና 19ኛው የባህል ፌስቲቫል ተጠናቋል። 

በውድድሩም በባህል ስፖርት ውድድር የኦሮሚያ ክልል አጠቃላይ አሸናፊ ሲሆን አማራ ክልልና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 2ኛ እና 3ኛ ሆነዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በባህል ፌስቲቫል በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ  ኦሮሚያና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች 2ኛ እና 3ኛ ሆነዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችሏል። 

በመርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ህይወት መሀመድ፡ የዘንድሮው የኢትዮጵያ የባህልና ስፖርቶች ውድድር ህብረ ብሄራዊ አንድነትና ሀገራዊ መስተጋብርን በአንድ መድረክ ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የሐረሪ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙራድ አብዲ በበኩላቸው፤ በክልሉ የባህል ስፖርት እና ፌስታቫል  መዘጋጀቱ መነቃቃትን ፈጥሯል ብለዋል። 

መርሃ ግብሩ ከስፖርት መድረክነት ባለፈ የህዝቦች ትስስርን በማጠናከርና መሠረተ ልማቶችን ማስተዋወቅ ያስቻለ መሆኑንም ገልጸዋል። 

አሸናፊ የነበሩ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ከእለቱ የክብር እንግዳና በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳና የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ወይዘሮ ህይወት መሀመድ እጅ የተዘጋጀላቸውን የዋንጫ ሽልማት ተረክበዋል። 

24ኛውን የባህል ስፖርቶች ውድድር እና የባህል ስፖርት ፌስቲቫልን የሲዳማ ክልል እንዲያሰናዳ መመረጡም ይፋ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም