ቀጥታ፡

ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ዕድገት የተሻለ የፖሊሲ አማራጭ ያቀረበን የፖለቲካ ፓርቲ  ለመምረጥ ካርድ ወስደናል - ነዋሪዎች

ድሬደዋ ፤መጋቢት 27/2018 (ኢዜአ)፦ ለሀገር  ዘላቂ ሰላምና ዕድገት  የተሻለ የፖሊሲ  አማራጭ ያቀረበን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን  የድሬዳዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

ለዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ በድሬዳዋ አስተዳደር በተዘጋጁት የምርጫ ጣቢያዎች ነዋሪዎች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በአካልና በዲጂታል አገልግሎት እያወጡ ይገኛሉ።

 ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት  ዕድሜያቸው ለመራጭነት የደረሱ ዜጎች   የምርጫ ካርዳቸውን በመውሰድ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መክረዋል።

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመሳተፍ ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ዕድገት  የሚበጅ አማራጭ ፖሊሲ ያቀረበን  የፖለቲካ ፓርቲን ለመምረጥ ካርድ አውጥተዋል።


 

አቶ ገዛኸኝ ተክሌ፤ ምርጫ ለሀገር ዴሞክራሲያዊ ስርአት መዳበር እና ለመድበለ ፓርቲ ስርአት መጠናከር አበርክቶው የጎላ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም  የመምረጥ ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ለመጠቀም የሚያስችላቸውን  የመራጭነት  ካርድ ማውጣታቸውን ተናግረዋል ።

ወይዘሮ ትዕግስት መዝገቡ በበኩላቸው፤ የምርጫ ካርዳቸውን  በማውጣት  የመምረጥ  መብታቸውን ለማረጋገጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረው ሌሎችም የዜግነት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ከልምዳቸው መክረዋል።


 

እሳቸውም  በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ፍፁም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ተአማኒ ምርጫ ሆኖ እንዲጠናቀቅ  ሚናቸውን  እንደሚወጡም  አክለዋል ።

አቶ ወንደውሰን ደምሴ በበኩላቸው፤ በዘንድሮ 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እያቀረቡ የሚገኙትን የክርክር ሃሳቦች በመገናኛ ብዙሃን እየተከታተሉ መሆኑን ተናግረዋል።


 

እየተካሄዱ የሚገኙት ክርክሮች የዜጎችን የምርጫ ተሳትፎ እያሳደጉ መሆናቸውንም አንስተዋል።

ወጣት ኦብሳ አደም የዘንድሮ  ጠቅላላ ምርጫ  ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ  ወጣቶች የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው ብሏል።

እሱም ለመራጭነት የሚያበቃውን ካርድ  መውሰዱን ጠቅሶ በመጪው ግንቦት በሚካሄደው ምርጫ ለድሬዳዋ ብሎም ለሀገር ዕድገት  ይሰራል የሚለውን ፓርቲ እንደሚመረጥ ገልጿል ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መርሃግብር መሠረት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም