ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል በለውጡ ዓመታት ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎች ተከናውነዋል

ሐረር ፤መጋቢት 27/2018 (ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል በለውጡ ዓመታት ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት  ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

በሐረሪ ክልል ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ ማደራጃ ማዕከል በሙሉ አቅሙ ተደራጅቶ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

በከተማው በሚገኘው አብርሃ ባህታ የተሃድሶ ህክምና ማዕከል የሚገኘው ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ ማደራጃ  ማዕከል ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት አቋርጦ የነበረ ሲሆን የክልሉ ጤና ቢሮ በሰው ሃይልና ቁሳቁስ ዳግም በማደራጀት በአዲስ መልክና በሙሉ አቅም ለአገልግሎት አብቅቷል።


 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማና በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሁርያ አሊ ማዕከሉን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በወቅቱ እንደገለፁት፤ በክልሉ ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ተግባራት ተከናውነዋል።

በክልሉ የተከናወኑ ስራዎችም ክልሉን ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ ያሻገሩና የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆኑን አመልክተዋል።


 

አክለውም የአካል ጉዳት ተጎጂ የሆኑ ዜጎችን የመደገፍ፣ የመንከባከብና በልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማስቻል ስራም ተከናውኗል ብለዋል።

በክልሉ የነበረው የሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ ማደራጃ ማዕከል ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት ሳይሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ማዕከሉ እንደገና አገልግሎት መጀመሩ  የአካል ድጋፍ ህክምና የሚፈልጉ ተገልጋዮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ማዕከሉ በዘላቂነትና ቀጣይነት ባለው መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ መንግስት ከሚያከናውነው ስራ ጎን ለጎን ባለድርሻ አካላትም አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ እንደገና አገልግሎት መስጠት መጀመሩ አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

ከዚህ ጎን ለጎን ማዕከሉ የተሟላና ሁሉንም ዓይነት የጤና አገልግሎቶች  እንዲሰጥ የማስቻል ስራ በቀጣይ ይከናወናል ብለዋል።

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሁርያ አሊ፤ ማዕከሉ  በአዲስ መልክ ታድሶና ተገቢው ግብዓት ተሟልቶለት ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉ የሚያስደስት ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።


 

ማዕከሉ አካል ጉዳተኞች የሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ በማደራጀት በልማቱ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በቀጣይም በክልሉ ኤረር ወረዳ ኡላን ኡላ ቀበሌ የተገነባውን 2ኛ ደረጃ ጤና ኬላን መርቆ አገልግሎት የማስጀመርና በድሬ ጠያራ ወረዳ አዲስ ለሚሰራው የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የመሰረት ድንጋይ የማኖር ስነ ስርዓት ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም