የታዳሽ ሃይልን በመጠቀም ለገጠሩ ህብረተሰብ የሃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የታዳሽ ሃይልን በመጠቀም ለገጠሩ ህብረተሰብ የሃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል
ባህርዳር ፤መጋቢት 27/2018 (ኢዜአ)፦ የታዳሽ ሃይልን በመጠቀም የገጠሩን ህብረተሰብ የሃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት መስጠቱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ "በብሄራዊ የኤሌክትሪፍኬሽን ፕሮግራም" አተገባበር ላይ ያተኮረ የሁለት ቀናት ስልጠና በባህርዳር ከተማ አስጀምሯል።
በሚኒሰቴሩ የኢነርጂ ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ኢንጅነር ሱልጣን ወሊ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለፁት ኢትዮጵያ በሃይድሮ፣ በፀሃይ፣ በነፋስና በጂኦተርማል ሃይል ማመንጨት የሚያስችል ከፍተኛ አቅም አላት።
ከነዚህ ዘርፎች ብቻ 150 ጊጋ ባይት ሃይል የማምረት አቅም ያላት ቢሆንም እስካሁን ወደ ልማት የገባው ግን ስድስት በመቶው ብቻ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህን የመልማት አቅም ወደ ውጤት ለመቀየር ከተደረጉ ጥረቶች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ሌሎች ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።
የታዳሽ ሃይልን በመጠቀም የገጠሩን ህብረተሰብ የሃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል።
ሀገሪቱ ለጀመረችው ፈጠን እድገት የሚያስፈልግን የሃይል አቅርቦት ለማሳካትና ብሄራዊ "የኤሌክትርፍኬሽን ፕሮግራም" ትግበራን በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ ለታዳሽ ሃይል ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።
በተለይም በፀሃይ ሃይል የሚሰሩ የሃይል አማራጮችን በስፋት በገጠሩ ለሚኖረው ህብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ በሚደረገው ሂደት የዛሬው ስልጠና አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ኢንጅነር ዳኝነት ፈንታ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሃይል አቅርቦትን ተደራሽነትን በማሳካት የክልሉን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ለማፋጠን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ይህም ከተሞችን ለማዘመን፣ ኢንዱስትሪዎችና ሌሎች ኢንቨስትመንቶችን ለማስፋፋት መሰረት በመሆን የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተጨማሪ አቅም ይሆናል ብለዋል።
በክልሉ በተራራቀ አሰፋፈር የሚኖረውን የገጠሩን ማህበረሰብ የሃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ በፀሃይ ሃይል ለሚሰሩ የኤሌክትሪክ መሰረት ልማት ዝርጋታ ላይ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ስልጠና የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የሶላር ፓኔል አቅራቢዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።