የግብርናው ዘርፍ እመርታ በቤተሰብ ደረጃ የአርሶና አርብቶ አደሩን ብልፅግና እያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የግብርናው ዘርፍ እመርታ በቤተሰብ ደረጃ የአርሶና አርብቶ አደሩን ብልፅግና እያረጋገጠ ነው
አዲስ አበባ፤መጋቢት 27/2018 (ኢዜአ)፦የግብርናው ዘርፍ እመርታ በቤተሰብ ደረጃ የአርሶና አርብቶ አደሩን ብልፅግና እያረጋገጠ እንደሚገኝ የክልል የግብርና ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ የብዝኅ ኢኮኖሚ የልማት አቅጣጫ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ታሪካዊ ስኬት እያስመዘገበ ይገኛል።
ለአብነትም በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በመኸርና በበልግ የሰብል ምርታማነት ወቅቶች የአርሶና አርብቶ አደሩን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ከፍተኛ ዕድገት ተመዝግቧል።
ይህም የኢትዮጵያን የተመፅዋችነት የታሪክ ስብራት በማረም ከራስ አልፎ ስንዴን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ያስቻለ አቅም ፈጥሯል።
የክልል ግብርና ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች ለኢዜአ እንዳሉትም፤ በከተማና ገጠር በግብርና ዘርፍ የተፈጠረው የምርታማነት አቅም የአርሶና አርብቶ አደሩን የኑሮ ደረጃ እያሻሻለ ነው።
በሀገራዊ ለውጡ ማግስት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተተገበሩ የግብርና ምርታማነት ተነሳሽነቶችም የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ መሰረት መጣላቸውን ገልጸዋል።
የአርሶና አርብቶ አደሩ ዘመናዊ የምርታማነት ሥርዓትም የግብርና ሽግግርን በማፋጠን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አሕመድ ሃቢብ እንዳሉት፤ ሀገራዊ ለውጡ የግብርና ዘርፉን በማዘመን የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ጉዞ እያፋጠነ ነው።
የብዝኅ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫዎችም የግብርና ሽግግርን በማሳለጥ በቤተሰብ ደረጃ የተሟላ ብልፅግናን እያረጋገጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ተግባራዊ የተደረጉ የአርሶና አርብቶ አደሩን ግብርና የማዘመን የልማት መርሃ ግብሮችም እመርታዊ ስኬት ማስገኘታቸውን አስረድተዋል።
በቀጣይም በሌማት ትሩፋትና በሰብል ምርታማነት የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠል የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ሥራ ለማፋጠን በትኩረት እንደሚሰራ አንስተዋል።
በአፋር ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አሕመድ አሚን በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ለውጡ የኢትዮጵያን ግብርና ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ ያስቻለ ስኬት አስገኝቷል ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋትና የስንዴ ልማት መርሃ ግብሮች የክልሉን ከፊል አርሶና አርብቶ አደር ማህበረሰብ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ምርታማነትን እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።
የኩታ ገጠም ሜካናይዜሽን የእርሻ ልማት መርሃ ግብርም የግብርና ግብዓት አቅርቦት ሰንሰለትን በማሳለጥ ወሳኝ የምርታማነት አቅም እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።