የኢትዮጵያ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት በዓለም አቀፍ ገበያ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት በዓለም አቀፍ ገበያ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ ነው
አዲስ አበባ፤መጋቢት 27/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ለውጡ ለኢትዮጵያ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርታማነት የሰጠው ትኩረት የዘርፉን ዓለም አቀፍ የገበያ ተወዳዳሪነት ማሳደጉን አምራችና ላኪዎች ገለጹ።
የሆርቲካልቸር ዘርፍ የዓለም አቀፍ ገበያ የተወዳዳሪነት አቅም ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ በማስገኘት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የድርሻውን እያበረከተ ይገኛል።
የአበባ፣የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች ለኢዜአ እንዳሉት፤በሀገራዊ ለውጡ ማግስት የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነትን እያሳደገ ነው።
የኢቲ ሃይላንድ ፍሎራ አበባ አምራችና ላኪ ሥራ አስኪያጅ እመቤት ተስፋዬ፤ ለሆርቲካልቸር የተሰጠው ትኩረት የአበባ ምርታቸውን በአውሮፓና አሜሪካ ገበያ የሚያቀርቡበት ወሳኝ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የአበባ ምርት የዓለም አቀፍ የገበያ ተፈላጊነት እያደገ መምጣቱም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ከቲንግ ሲንጀንታ ፍላወር ሳይት ማናጀር መስፍን ግርማ በበኩላቸው፥የኢትዮጵያ የአበባ ምርት በተለያዩ ክፍለ አህጉራት ያለው ከፍተኛ ተፈላጊነት የገበያ መዳረሻ ዕድልን አስፍቷል ብለዋል።
በመንግስት በኩል በመሬት አቅርቦትና ተያያዥ መሠረተ ልማት ግንባታ የተሰጠው ትኩረት ምርታማነትን በማሳደግ የገቢ አቅም እያጎለበተ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም የአበባ ምርታማነት አቅምን በማስቀጠል በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካኝነት ምርትን በጥራትና በፍጥነት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የሬድ ፎክስ ኢትዮጵያ ዱመኖሬንጅ አበባ ላኪ ማናጀር ራሄል ክፍሌ በበኩላቸው፤አውሮፓ፣ አሜሪካና የእስያ ገበያ የኢትዮጵያ የአበባ ምርት ወሳኝ የገበያ መዳረሻዎች ናቸው ብለዋል።
ይህም የውጭ ምንዛሬ ገቢን በማሳደግ የአበባና ሆርቲካልቸር ዘርፍ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዲጎለብት እያስቻለ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንዳለ ሃብታሙ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን የሆርቲካልቸር ዘርፍ ኢንቨስትመንትና ምርታማነት የሚያጎለብት ምቹ ምኅዳር ተፈጥሯል ብለዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር በዓለም ገበያ ያለው ተፈላጊነት የውጭ ምንዛሬ ገቢን በማሳደግ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ የላቀ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በአበባ፣አትክልትና ፍራፍሬ ወጪ ንግድ የምታስገኘው ስኬት የሥራ ዕድል ፈጠራና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርን እያፋጠነ መሆኑን አንሰዋል።