የመጋቢት 24ቱ ለውጥ ሀገሪቷን ከተደቀኑባት ትላልቅ ስጋቶች ያተረፈ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመጋቢት 24ቱ ለውጥ ሀገሪቷን ከተደቀኑባት ትላልቅ ስጋቶች ያተረፈ ነው
ጅግጅጋ፣መጋቢት 27/2018(ኢዜአ)፦የመጋቢት 24ቱ ለውጥ ሀገሪቷን ተደቅነውባት ከነበረ ውስጣዊና ውጫዊ ስጋቶች ያተረፈ ነው ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሀመድ ሻሌ ገለጹ።
የመጋቢት 24ቱ ሀገራዊ ለውጥ 8ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሀመድ ሻሌ በህዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ እንደገለጹት፣ የመጋቢት 24ቱ ለውጥ የክልሉ ሠላምና ልማት የተጠናከረበት እና ህብረ ብሔራዊ አንድነት የጎለበተበት ነው።
በተለይም የሶማሌ ክልል ቀደም ሲል ከነበረበት የሠላምና ልማት ችግር ወጥቶ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎን ያረጋገጠበት ነው ብለዋል።
እለቱ ኢትዮጵያን ተደቅነውባት ከነበረው ውጫዊና ውስጣዊ ስጋቶች ያተረፈ መሆኑን ገልጸው፤ መጋቢት 24 ክልሉም በሀገሪቷ ፖለቲካዊ እኩል ተሳትፎ ያሳደገበት መሆኑን ነው ያነሱት።
በለውጡ አመታት በሀገሪቷ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች የተጀመረበት እና የተጠናቀቀበት መሆኑንም ገልጸዋል።
የጅግጅጋ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ሻፊ አህመድ በበኩላቸው፥ የመጋቢት 24 ለውጥ የዜጎች የሠላም፣የልማትና የመልካም አስተዳደር ተሳትፎ የተቀየረበትና የህዝቡን ችግሮች የፈቱ የልማት ሥራዎች የተከናወኑበት ነው ብለዋል።
ከለውጡ በፊት ክልሉ የሠላም ፤ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ችግሮች የነበረበት እንደነበረ አንስተው፤ከለውጡ በኋላ ወደ ልማት በመግባት የብልጽግና ተምሳሌት ሆኗል ብለዋል።
የክልሉ ህዝብ ከስጋትና ፍርሃት የወጣበትና የሀገሪቷ የፖለቲካ ተሳትፎ የጨመረበት መሆኑንም አክለዋል።
ጅግጅጋ ከተማ የከተሞች ተምሳሌት እየሆነች መምጣቷን በመጥቀስ በሀገራዊ ለወጡ የተገኘው ሠላም እና ልማትን ለማስቀጠል ህዝቡ ተሳትፎውን እንዲያስቀጥልም አሳስበዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ መጋቢት 24 ታሪካዊ ቀን የሚታወስበት ነው፤ የድልም ትሩፋት የተገኘበትና ሠላማችን የተረጋገጠበት ቀን ነው የሚሉና ሌሎች መልዕክቶች ተላልፈዋል።