ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ተችሏል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2018 (ኢዜአ)፦በሀረሪ ክልል ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ያስቻሉ ስራዎች መሰራታቸውን የሐረሪ ክልል ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ገለፀ።


 

የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሄኖክ ሙሉነህ  እንደገለጹት ባለፉት ስምንት የለውጥ አመታት በሐረሪ ክልል በየዘርፉ ተጨባጭ ውጤት ያመጡ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል። 

በክልሉ ከለውጡ ወዲህ ለግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በተሰሩ ስራዎች ውጤት ከተመዘገበባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል።

አርሶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅና ያሉ ውስን መሬት በዘር እንዲሸፈን ለአርሶ አደሩ ከስልጠና ጀምሮ አስፈላጊ ግብዓቶችን በማቅረብና በመደገፍ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ለማስቻል ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተከናውነዋል። 

ሰፋፊ የመስኖ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክቶች በመገንባት አርሶ አደሩ በመስኖ እንዲያለማ የሚያስችል ስራ ተከናውናል። 

በተለይም በሰብልና በእንስሳት ምርትና ምርታማነትን፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እንዲሁም በመስኖ ግንባታ ዙሪያ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ማከናውን ተችላል። 


 

እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬዎች እና በሌማት ትሩፋት  የተከናወነው ስራም አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።

አርሶ አደሩ የሚያለማውን የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ስራዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለከተማው ማህበረሰብ በማቅረብ የዋጋ ንረቱን ከማረጋጋት ባለፈ ለአርሶ አደሩ የገበያ ትስስር እንዲያገኝ አስችሏል። 

በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃም በተግባር የተገለጡ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል። 


 

በክልሉ ከተማና ገጠር ወረዳዎች በሌማት ትሩፋት፣ በእንስሳት ተዋጽኦና በአትክልትና ፍራፍሬ የተከናወኑ ስራዎች ህብረተሰቡ የኑሮ ውድነት ጫናን ለማቃለልና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ አስችለዋል። 


 

በገጠር በመስኖ ልማት የተከናወኑ ስራዎችም ምርትና ምርታማነት እንዲጎለብትና የአርሶ አደሩ ምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ በማገዝ ረገድ ተጨባጭ ውጤት አስገኝቷል። 

በበልግና መኽር እርሻ የዝናብ እጥረትን ተቋቁመው በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ የበቆሎና የማሽላ እርሻ ስራ በእጥፍ እንዲያድግና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ አስችሏል። 

በክልሉ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና እንክብካቤ የተከናወኑ ስራዎችም አርሶ አደሩ የከርሰ ምድር ውሃን በቅርበት እንዲያገኝ በማስቻሉ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቆ ምርትና ምርታማነቱ እንዲጎለብት አድርጓል። 

በቀጣይም የክልሉ መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ እና ምርትና ምርታማነት ለማጎልበት የሚያከናውናቸውን ስራዎች በላቀ ቁርጠኝነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

#Ethiopian_News_Agency  #ኢዜአ  #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም