በተጠባቂው መርሐ ግብር ባርሴሎና አትሌቲኮ ማድሪድን በመርታት በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
በተጠባቂው መርሐ ግብር ባርሴሎና አትሌቲኮ ማድሪድን በመርታት በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018 (ኢዜአ)፦ በስፔን ላሊጋ የ30ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ ባርሴሎና አትሌቲኮ ማድሪድን 2 ለ 1 አሸንፏል።
ማምሻውን በዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጁሊያኖ ሲሞኒ በ39ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል መሪ መሆን ችሏል።
ማርከስ ራሽፎርድ በ42ኛው ደቂቃ ባሳረፈው ግብ ባርሴሎና አቻ ሆኗል።
ተቀይሮ የገባው ሮበርት ሌዋንዶውስኪ በ87ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ጎል ለባርሴሎና ወሳኝ ሶስት ነጥብ አስገኝቷል።
የአትሌቲኮ ማድሪዱ ኒኮላስ ጎንዛሌዝ በመጀመሪያው አጋማሽ ማብቂያ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
የባርሴሎናው ጄራርድ ማርቲን ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ 46ኛው ደቂቃ ቀይ ካርድ ቢመለከትም በቪዲዮ በታገዘ ዳኝነት ታይቶ የመጀመሪያ ውሳኔ ተሽሮ ወደ ቢጫ ካርድ ተቀይሯል።
የቀይ ካርዱ መሻር የአትሌቲኮ ማድሪድ የቡድን አባላት እና ደጋፊዎችን ያስቆጣ ሲሆን ማርቲን በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ ሜዳ መውጣት ነበረበት በሚል ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ባርሴሎና ያገኘውን የቁጥር ብልጫ ተጠቅሞ በፈጠረው ጫና ግብ አስቆጥሯል።
ጨዋታው ጉልበት የተቀላቀለበት መሆኑ በርካታ ቢጫ ካርዶች እንዲመዘዙ አድርጓል።
ውጤቱን ተከትሎ ባርሴሎና ነጥቡን ወደ 76 ከፍ በማድረግ መሪነቱን አጠናክሯል።
በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል። ከተከታዩ ሪያል ማድሪድ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሰባት ከፍ አድርጓል።
ባርሴሎና በሊጉ 25ኛ ድሉን አስመዝግቧል።
በአንጻሩ በሊጉ ሰባተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አትሌቲኮ ማድሪድ በ57 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
ሪያል ማድሪድ ዛሬ ባደረገው ጨዋታ በሪያል ማዮርካ ባልተጠበቀ ሁኔታ የ2 ለ 1 ሽንፈት አስተናግዷል።
ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ ረቡዕ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚያደርጉት የሩብ ፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ይጠበቃል።