አርሰናል ከኤፍኤ ካፕ ውድድር ውጪ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
አርሰናል ከኤፍኤ ካፕ ውድድር ውጪ ሆነ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018 (ኢዜአ)፦ በኤፍኤ ካፕ ሶስተኛ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ሳውዝሃምፕተን አርሰናልን 2 ለ 1 አሸንፏል።
ማምሻውን በሴንት ሜሪ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሮስ ስቲዋርት እና ሼ ቻርልስ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ቻርልስ በ85ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ያሳረፈው ጎል ሳውዝሃምፕተን አሸናፊ አድርጓል።
ለአርሰናል ቪክቶር ዮኮሬስ ብቸኛውን ግብ አስቆጥሯል።
በጨዋታው አርሰናል ብልጫ ወስዶ ቢጫወትም ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር አልቻለም።
ተጋጣሚው ሳውዝሃምፕተን ያገኛቸውን የግብ እድሎች በሚገባ ተጠቅሟል።
ውጤቱን ተከትሎ 14 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ስኬታማ የሆነው አርሰናል በሩብ ፍጻሜው ተሰናብቷል።
ለአራት ዋንጫዎች ሲፎካከር የነበረው አርሰናል የሚፎካከርባቸው ዋንጫዎች ብዛት ወደ ሁለት ዝቅ ብለዋል።
በእንግሊዝ ሁለተኛ ዲቪዚዮን (ሻምፒዮንሺፕ) የሚገኘው ሳውዝሃምፕተን ሳይጠበቅ ወደ ግማሽ ፍጻሜ አልፏል።
ዛሬ በተደረጉ ሌሎች የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ማንችስተር ሲቲ ሊቨርፑልን 4 ለ 0፣ ቼልሲ ፖርት ቫሌን 7 ለ 0 በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ አልፈዋል።