አዲስ ስፖርት ፓርክ የመደመር እሳቤና ተግባር የታየበት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ ስፖርት ፓርክ የመደመር እሳቤና ተግባር የታየበት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018 (ኢዜአ)፦ አዲስ ስፖርት ፓርክ የመደመር እሳቤና ተግባር የተገናኙበት ፕሮጀክት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የአዲስ ስፖርት ፓርክ ዛሬ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ፓርኩ የኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍ ልማት በተግባር የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢኮኖሚ ልማት ያለ ሰብአዊ ልማት ምልዑ ሊሆን እንደማይችል ጠቁመው፣ የስፖርት መሠረተ ልማት ማስፋፊያዎች የዚሁ የሰው ተኮር ልማት ተግባር ማሳያ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የመደመር መንግሥት ዋና እሳቤም ሁሉን አቀፍ ልማትን ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ መሆኑንና ዛሬ የተመረቀው ፓርክም ይህ እሳቤና ተግባር የተገናኙበት ትልቅ የስፖርት አውድ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ፓርኩ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የሁሉም ስፖርቶች መሠረተ ልማት እና የአረንጓዴ መዝናኛ ስፍራዎችን አሟልቶ የተገነባ ነው ብለዋል።
ይህም ስፍራ ለወጣቶች መወዳደሪያና ለታዳጊዎች መጎልበቻ ከመሆኑ ባለፈ፣ ለሀገራቸው ትልቅ ክብር ያመጡ የስፖርት ፈርጦች ሐውልት የቆመበት የጀግኖች አምባ ሆኖ እንዲያገለግል ተደርጎ መዘጋጀቱን ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመለከቱት።
በተለይም በፓርኩ ውስጥ የጀግኖች ገጽታ ከነጽናታቸውና ከነአርዓያነታቸው፣ እንዲሁም ፊታቸው ላይ ከተጻፈው የሀገር ፍቅር ጋር ተደምሮ በሐውልት መታሰቢያነት መቆሙን አንስተዋል።
ሐውልቶቹ ለኢትዮጵያ የሮጡ እግሮችንና ለሀገር የተከፈለ ውድ ዋጋን በሚዘክር መልኩ በክብር ተቀርጸው የተቀመጡ መሆናቸውንም እንዲሁ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአዲስ ስፖርት ፓርክ መመረቅ መንግሥት ለሕዝብ የገባውን ቃል እያከበረና ኃላፊነቱን እየተወጣ ስለመሆኑ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ቃል ተግባር እየሆነ አዲስ አበባም እየተቀየረች፣ ኢትዮጵያም ወደ ክብር ማማ እየገሰገሰች ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።