ቀጥታ፡

ባሳለፍነው ሳምንት …

ከመጋቢት 20 እስከ መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም ከተከናወኑ ዐበይት ጉዳዮች መካከል

•  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ስለ አዲስ አበባ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት ባስተላለፉት መልዕክት፤ አዲስ አበባ ከዋና ከተማ በላይ መሆኗን ገልጸው፤ በፈጣን እንቅስቃሴ ላይ ያለች፣ ወደ ኢትዮጵያ ነገ የመግቢያ በር፣ በፍጥነት እየተለወጠች ያለች የሀገር የልብ ትርታ፣ ሁሉንም አሳታፊ እና አርቆ አሳቢ የሆነ የከተማ ልማት ትልማችን መገለጫ ናት ብለዋል።

ፈጣን መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት፣ የዘመናዊ ከተማ መፍትሔዎችን በማቅረብ፣ አካታች በሆነ መልኩ መኖሪያ ቤት በመገንባት እና ዘላቂ ዕድገትን በማረጋገጥ እየሠራን ያለነው ዛሬን ብቻ ሳይሆን ለነገው ትውልድ ጭምር ነው ሲሉም አስገንዝበዋል። በኢትዮጵያ የሚገኙ ከተሞቻችን ሰዎችን ለማብቃት፣ ዐቅምን ለመጠቀም እና ዘላቂ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ቅርጽ ይዘዋልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

•  አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ዘመናዊ የምርምር ማዕከል መመረቅ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የሳይንስ ሥነ-ምሕዳር ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ዘመናዊ የምርምር ማዕከል መርቀው ከፍተዋል።

በአርማወር ሐንሰን የምርምር ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባው ይህ ዘመናዊ ተቋም ከመሠረተ ልማት ግንባታ ባለፈ፤ ራሷን የቻለችና ጤናማ የሆነች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚተጋ የላቀ የዕውቀት ማዕከል ነው ብለዋል በወቅቱ።

የምርምር ማዕከሉ 40 ላቦራቶሪዎችን፣ የላቁ የጂኖሚክስ (genomics) እና የባዮኢንፎርማቲክስ (bioinformatics) ቦታዎችን እንዲሁም በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶችን ጥራትና ብቃት የሚያረጋግጥ የባዮኢኩዊቫለንስ (bioequivalence)  ማዕከል ማከተቱን አብራርተዋል።

ምርምርን ወደ ፖሊሲ፣ ፈጠራን ደግሞ ወደ ተግባራዊ መፍትሔ በመቀየር፤ ይህ ማዕከል በመድኃኒት ምርት ራሳችንን ለመቻል፣ ዘላቂ የጤና ደህንነትን ለማረጋገጥ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ እስካሁን ያስመዘገብናቸውን ስኬቶች ይበልጥ ለማሳደግ የሚረዳ ትልቅ እርምጃ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።

  የአዲስ ስፖርት ፓርክ መመረቅ

ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የከተማችንን እድሳት ለማፋጠን እና የዜጎቻችንን ክብር ለመመለስ የገባነውን ቃል አንዱ ማረጋገጫ የሆነውን የአዲስ ስፖርት ፓርክን በይፋ መርቀን ከፍተናል ብለዋል።

በ5 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ፕሮጀክት፤ በኦሎምፒክ መድረክ ለሀገራችን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኙ 15 አትሌቶችን የሚዘክሩ የክብር ሐውልቶችን በፓርኩ መሃል በማቆም፣ የጀግኖቻችን ታሪክ ለተተኪ ትውልድ ስፖርተኞች ተምሳሌት ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጋልም ነው ያሉት።

የኦሎምፒክ ደረጃውን የጠበቀ የመዋኛ ገንዳ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የእግር ኳስ፣ የቅርጫት ኳስና የሜዳ ቴኒስ መሰረተ ልማቶች እንዲሁም የ800 ሜትር የሩጫ ትራክን ጨምሮ፤ እያንዳንዱ የዚህ ማዕከል ክፍል የዓለም አቀፍ መስፈርቶችን እንዲያሟላ ተደርጎ ተገንብቷል ሲሉም ገልፀዋል።

  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በአፋር

ባሳለፍነው ሳምንት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአፋር ክልል ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤ በዚሁ ወቅት በአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ በመሥኖ እየለማ ያለው የሱፍ ምርት ለተሻገረ ግብርና እና ለተሻገረ ገጠር ራዕያችን ተደማሪ ሃብት ነው ብለዋል።

በአፋር ክልል ያየነው በመሥኖ ተፋሰስ በረሃ የመሰለውን ምድር የምርት መትረፍረፊያ የማድረግ ትጋት፤ ለሌሎች በተለይም ከዓመት እስከ ዓመት ዝናብ አጠር አካባቢዎች ትልቅ የመማሪያ ሠነድ እንደሚሆን አመላክተዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በተካሄደው "የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ቅንጅት ለሀገራዊ ሰላም እና ደኅንነት" በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው ብሔራዊ የደኅንነት ኮንፈረንስ ላይ የተሳተፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፤ በዚሁ ወቅት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች የጸጥታና ደኅንነት ተቋሞቻችን ችግርን ወደ ዕድል እንዲቀየሩ ያስቻሉ ናቸው ብለዋል፡፡

ጉዟችን ተጀመረ እንጂ አልተቋጨምና ከትናንት ዕዳዎች ተላቀን፣ የዛሬ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን ለነገው ትውልድ የምትመጥን ሀገር ለመገንባት በዓላማ ጽናት እንቀጥላለን ሲሉም አመላክተዋል።

  ስለ መጋቢት 24  

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ ሥልጣን የመጣውን የለውጡን መንግሥት የሚደግፉ ሕዝባዊ ሰልፎች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተካሂደዋል።

በእነዚህ ሰልፎች ላይም መንግሥት ባለፉት ሥምንት ዓመታት ያመጣቸውን ለውጦች እና የተገኙ ስኬቶችን የሚያወሱ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም (ዶ/ር) ለሰጡት ስኬታማ አመራርነት የሚያሞግሱና የሚያመሠግኑ መልዕክቶች ተስተጋብተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ቀኑን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሕዝባዊ ግፊትና ትግል ያመጣው የመጋቢት ለውጥ ኢትዮጵያን ወደ ኋላ ያስቀሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ስብራቶችን መጠገን ያስቻሉ ሪፎርሞች የተተገበሩበት ነው ብለዋል። ለሕዝባችን የላቀ ተጠቃሚነት፣ ለሀገራችን ክብርና ብልፅግና መሳካት አበክረን እንሠራለን ሲሉም ገልጸዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በበኩሉ ቀኑን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በኃይልና በምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ አስደማሚ ስኬቶችን አስመዝግባለች ብሏል።

የለውጡን መሠረት ከማስፋትና ከማጽናት ወደ ማላቅ የተሸጋገረችው ኢትዮጵያ፤ በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌትነቷን በተግባር ታውጃለች ሲልም ገልጿል። ይህን ለውጥ ዕውን ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፤ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ በድል እንደሚያሳርጉት ጥርጥር የለውም ነው ያለው።

  የ13 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር የኢንቨስትመንት ስምምነት

የኢትዮጵያ መንግሥት በInvest in Ethiopia 2026 ፎረም፤ ከቻይና፣ ፖላንድ፣ ሕንድ፣ ሲንጋፖር እና ኬንያ ከመጡ አጋሮች ጋር የ13 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ታሪካዊ የኢንቨስትመንት ስምምነት መፈራረሙን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባሳለፍነው ሳምንት አስታውቋል።

በታዳሽ ኃይል፣ በማዕድንና በአረንጓዴ አሞኒያ ዘርፎች ላይ ያተኮሩት እነዚህ ስምምነቶች፤ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳችን ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ጉልህ ማሳያ ናቸው ብሏል።

በተመሳሳይ ጽሕፈት ቤቱ ባሳለፍነው ሳምንት ባጋራው መረጃ፤ ከ60 ዓመታት በላይ ያገለገለውን የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ የሚተካ የወንጀል ሥነ-ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1410/2018 ሆኖ መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል ብሏል።

የ1954 የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ለበርካታ አሥርት ዓመታት በሥራ ላይ የቆየ በመሆኑ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት እና ከወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ እንዲሁም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በዘርፉ ካሉ አዳዲስ አሠራሮችና የቴክኖሎጂ እድገቶች አኳያ ከዘመኑ ጋር በተጣጣመ መልኩ መከለሱ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ባለፉት ዓመታት የአዲስ ሕግ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።

ብዙ ምክክር ተደርጎበት የጸደቀው የሕግ መድብል አዳዲስ አሠራሮችን የሚያስተዋውቅ፤ የወንጀል ምርመራ፣ ክስና ማስረጃ ሥርዓቱን ወደአዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው ሲልም አስገንዝቧል ጽሕፈት ቤቱ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም