ቀጥታ፡

ሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎት ወቅቱን የዋጀ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018 (ኢዜአ)፦ ሞተር አልባ የትራንስፖርት አማራጭ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚስማማና ወቅቱን የዋጀ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ።

"የብስክሌት መጋራት" የትራንስፖርት አገልግሎት የማስጀመሪያ መርሀ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን፤ አገልግሎቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመስቀል አደባባይ ቦሌ ድረስ መሆኑም ተገልጿል።

ብስክሌቶቹ በሞባይል መተግበሪያ አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የጂፒኤስ ሲስተም እንደሚጠቀሙም በመርሀ ግብሩ ላይ ተመላክቷል።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎት ከአየር ንብረት ጋር ተስማሚ የትራንስፖርት አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል።

"የብስክሌት መጋራት" የትራንስፖርት አገልግሎቱ ወቅቱን የዋጀ ምላሽ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ለብስክሌት መጋራት የትራንስፖርት አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው፤ ለሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።

ዛሬ ይፋ የተደረገው የብስክሌት መጋራት የትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው፤ ሚኒስቴሩ በሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰማሩ አካላት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ሀላፊ ያብባል አዲስ በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳደሩ የሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኮሪደር ልማቱ ከ240 ኪሎ ሜትር በላይ የብስክሌት መንገድ መሰራቱን ጠቁመው፤ መሰረተ ልማቱንም በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ መጽደቁንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ስድስት የሚሆኑ የብስክሌት ኦፕሬተሮች ቅድመ ምዝገባ በማድረግ የዝግጅት ስራ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ዘርፉ የትራንስፖርት አገልግሎትን በጉልህ የሚያሻሽል መሆኑን ገልጸው፤ በሁሉም አካባቢዎች ለማስፋፋት በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸውም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የትራንስፖርት አገልግሎቱ ከመጀመሩ በፊት በተደረገ ሙከራ ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን መገንዘብ መቻሉን ያመለከቱት የአዲስ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ ሳተና ዋሬ ናቸው።

ለአገልግሎቱ የሚውለው መተግበሪያም በራስ አቅም በሀገር ልጆች መልማቱን ጠቁመዋል።

አገልግሎቱ የፋይዳ ቁጥር በማስገባት መጠቀም የሚቻል ሲሆን፤ ክፍያውም በዲጂታል መንገድ በሞባይል የሚፈጸም መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም አገልግሎቱን በተለያዩ አካባቢዎች ለማስፋት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በደንብ ቁጥር 183/2017 የብስክሌት መጋራት እና የብስክሌት መስመር አጠቃቀም ደንብ ማጽደቁ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም