ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚያስኬዱ የሕክምና አገልግሎቶችን በሀገር ውስጥ መስጠት የሚያስችል አቅም እየገነባች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚያስኬዱ የሕክምና አገልግሎቶችን በሀገር ውስጥ መስጠት የሚያስችል አቅም እየገነባች ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚያስኬዱ የሕክምና አገልግሎቶችን በሀገር ውስጥ መስጠት የሚያስችል አቅም እየገነባች መሆኑን የዘርፉ ተዋናዮች ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያደረገችው ያለው የቴክኖሎጂ ሽግግር የሜዲካል ቱሪዝምን የሚያሳልጥ መሆኑም ተመላክቷል።
በአዲስ አበባ እየተካሄዱ የሚገኙት ሁለተኛው የሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓት ምርትና ኢኖቬሽን ኤግዚቢሽን እንዲሁም 10ኛው የኢትዮ ኸልዝ ዓለም አቀፍ የሕክምና ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይና ጉባኤ የሀገሪቱን የጤና ዘርፍ ስኬቶች አጉልተው አሳይተዋል።
በኤግዚቢሽኑ የተሳተፉ የሕክምና መሣሪያ አምራቾችና አስመጪዎች እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የጤና ዘርፉን ለማዘመን በሰጠችው ልዩ ትኩረት ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል።
የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ቀደም ሲል በሀገር ውስጥ የማይታሰቡ ዘመናዊ የሕክምና ቁሳቁሶችን በማሟላት ውጤታማ ሕክምና መስጠት መጀመራቸውን ጠቁመዋል።
የበርለ ኦፍ ሜዲካል ካምፓኒ ተወካይ ዶክተር ኪሩቤል ክፍሌ፥ የኢትዮጵያ ጤና ዘርፍ እያሳየ ያለው እድገት እጅግ ፈጣንና አስገራሚ መሆኑን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ትኩረቱ በተላላፊ በሽታዎች ላይ ብቻ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ሆስፒታሎች ውስብስብ ሕክምናዎችን በሀገር ውስጥ መስጠት የሚያስችሉ ትልልቅ ማሽኖችን ታጥቀዋል ብለዋል።
ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዜጎች ለሕክምና ወደ ውጭ ለመሄድ ይገደዱባቸው የነበሩ ህክምናዎችን በሀገር ውስጥ ለመስጠት አቅም በመፍጠር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያድን ጠቅሰዋል።
የቻይናው ሰንሼን ማኑፋክቸሪንግ ድርጅት የኢትዮጵያ ካንትሪ ማናጀር አማኑኤል ሽጉጥ በበኩላቸው፤ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የታገዙና የሐኪሞችን ሥራ የሚያቀሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አንጻር በዘርፉ ያላትን ተወዳዳሪነት ከፍ የሚያደርገውና የሜዲካል ቱሪዝምን የሚያሳልጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ የሕክምና ኤግዚቢሽኖች በኢትዮጵያ መካሄድ መጀመራቸውም ለዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
መንግሥት ለጤናው ዘርፍ እያደረገ ያለው ከፍተኛ ድጋፍና ለሕክምና መሣሪያዎች ግዢ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ላይ ቅድሚያ መስጠቱ ለዚህ ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን የተናገሩት ደግሞ ከዓለም ኢንተርናሽናል ፒኤልሲ የመጣው የባዮ ማዲካል ኢንጂነር አስቻለው አሸናፊ ናቸው።
በተጨማሪም የሕክምና መሣሪያዎች በጥብቅ ቁጥጥር እንዲገቡ መደረጉ ጥራታቸውን የጠበቁ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ አስችሏል ብለዋል።
በቀጣይም በሀገር ውስጥ ያለውን የማምረት አቅም በመጠቀም ወደ ማምረቱ ሥራ ይበልጥ መግባት ለዘርፉ እድገት ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።