ቀጥታ፡

ሲዳማ ቡና በመሪነት ግስጋሴው ቀጥሏል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018 (ኢዜአ)፦‎ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሲዳማ ቡና መቀሌ 70 እንደርታን 1 ለ 0 አሸንፏል። 

ማምሻውን በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አቤል ያለው በ25ኛ ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና ነጥቡን ወደ 48 ከፍ በማድረግ መሪነቱን አጠናክሯል። ከተከታዩ ሃዋሳ ከተማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ስምንት ከፍ ማድረግ ችሏል።

ቡድኑ በአጠቃላይ በውድድር ዓመቱ ያሸነፋቸው ጨዋታዎች ብዛት 13 ደርሰዋል።

በአንጻሩ በሊጉ 10ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው መቀሌ 70 እንደርታ በ23 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አላሸነፈም። 

የሲዳማ ቡናው አቤል ያለው በሊጉ ከመረብ ላይ ያሳረፋቸውን ጎሎች ብዛት ወደ 11 ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ነው።

ዛሬ ቀን ላይ በተደረጉ የ25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀዲያ ሆሳዕናን 2 ለ 1፣ ኢትዮጵያ ቡና ኢትዮጵያ መድንን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።

ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም